ከትግራዩ ትህነግ ጋር አብረን እንሰራለን፤ ከጎጃሙ አማራ፤ የአማራ ፋኖ ህዝባዊ ድትጅት በጎጃም እዝ ጋር ግን አብረን አንሰራም፤ የገቡበት ገብተን የማያዳግም እርምጃ እንወስድባቸዋለን ....አስረስ ማረ ዳምጤ ፤ በወንድወሰን ተክሉ
ከትግራዩ ትህነግ ጋር አብረን እንሰራለን፤ ከጎጃሙ አማራ፤ የአማራ ፋኖ ህዝባዊ ድትጅት በጎጃም እዝ ጋር ግን አብረን አንሰራም፤ የገቡበት ገብተን የማያዳግም እርምጃ እንወስድባቸዋለን ....አስረስ ማረ ዳምጤ
በጎጃም ምድር ተሸሽጎ ከትህነግ ጋር እየተባበረ በጎጃም ምድር በተወለዱ ፋኖዎቻችን ላይ የሚዘምትን ውስጣዊን ጠላት መንጥረን ማጽዳት አለብን ‼️‼️‼️
ምስሉ ጸሃፊውን አይወክልም። |
በወንድወሰን ተክሉ
አስረስ ማረ ዳምጤ - የአማራ ፋኖ በጎጃም ፖለቲካ ዘርፍ ኃላፊ የትህነጉ መሪ ዶ/ር ደብረጺዮን ገብረሚካኤል በቅርቡ ከአማራ ፋኖ እና ከኤርትራው መንግስት ሻእቢያ ጋር አብረን ለመስራት እንፈልጋለን ለሚለው ገለጻው በብርሃን ፍጥነት ብቅ ብሎ «ከህወሃት ጋር አብረን እንሰራለን» በማለት ምላሽ ሰጥቷል፡፡ ይህ የአስረስ ማረ ዳምጤ ምላሽ የአንድ ግለሰብ ሳይሆን የድርጅቱ፤ ማለትም የአማራ ፋኖ በጎጃም ተብሎ የሚጠራ አንድ አደገኛ ተዋጊ ቡድን ድርጅታዊ አቌም መሆኑን መላው የአማራ ህዝብና መላው የአማራ ፋኖ አደረጃጀቶች በሙሉ ሊያውቁት የሚገባ እውነታ ነው፡፡
በእርግጥ የትህነጉ ዶ/ር ደብረጺዮን ከፋኖ ጋር አብሮ ለመስራት እንፈልጋለን የሚለው አሁናዊ አባባል ዝም ብሎ ከመሬት ተነስቶ የተነገረ ሳይሆን በሁለቱ ፋሺስታዊ ቡድኖች መካከል - ማለትም በዘመነ ካሴ በሚመራው የአማራ ፋኖ በጎጃም እና በዶ/ር ደብረጺዮን ገብረሚካኤል በሚመራው የትግራዩ ትህነግ መካከል በተካሄደ ምስጢራዊ ግንኙነትና ስምምነት መሰረት ዛሬ ዶ/ር ደብረጺዮን በአደባባይ የተናገሩት ሀቅ መሆኑን ማወቅና መረዳት ይገባል፡፡
ባለፈው ሀምሌ ወር ውስጥ የአማራ ፋኖ በጎጃም አመራር ነን የሚሉት አስረስ ማረ እና ማርሸት ጸሀዬ ከትግራዩ ትህነግ ከዶ/ር ደብረጺዮን ጋር ምስጢራዊ ንግግርና ድርድር ማድረጋቸውን ያጋለጥ የድምጽ ሪኮርድ ይፋ ማድረጋችን ይታወሳል፡፡
በዚያ ምስጢራዊ የስልክ ንግግር አስረስና ማርሸት ከደብረጽዮን ጋር ምስጢራዊ ንግግር፤ድርድርና ስምምነት ማድረጋቸውን በመግለጽ ከጌታቸው ረዳ ጋር ይቀረናል በማለት በሁለቱ ቡድኖች መካከል በአካል ተገናኝተው ጉዳዪን ለመቌጨት የመገናኛ ስፍራ፤ቦታና ግዜ በመምረጥ ላይ መሆናቸውን ሲገልጹ የሰማንበት አውዲዮ ሲሆን ያ ማለት በዘመነ ካሴ የሚመራው የአማራ ፋኖ በጎጃም የሚባለው ቡድን ከጎጃም ህዝብ፤ከአማራ ህዝብና ከመላው የአማራ ፋኖ ሀይሎች የተደበቀን ምስጢራዊን ግንኙነትን እና ስምምነትን ከትግራዩ ትህነግ ጋር ማድረጉን ያረጋግጥልናል፡፡
ከዚህ ምስጢራዊ ግንኙነትና ስምምነትና አንጻ ወያኔ በወልቃይት ጠገዴ፤ ጠለምትና በሰሜን ወሎ ራያ በኩል የትንኮሳ ወረራ በከፈተችበት ወቅት - ባለፈው ሰኔ ወር- የአማራ ፋኖ በጎጃም ቃለ አቀባይ ማርሸት ጸሀዬ በሚዲያ ብቅ ብሎ ወያኔ ተሳስታ ብትወረን እና ጦርነት ብትከፍትብን እንኳን እኛ መልሰን አንተኩስባትም በማለት በሁለቱ ፋሺስታዊ ቡድኖች መካከል መላው የአማራ ህዝብና መላው የአማራ ፋኖ ያለወቀው ምስጢራዊ ስምምነት መደረጉን ያረጋገጥንበት ክስተት ብለን መዝገበነዋል፡፡ ስለሆነም ይህንን ድብቅ ምስጢራዊ ግንኙነትና ስምምነትን መሰረት በማድረግ ባለፈው ሳምንት ዶ/ር ደብረጺዮን ከፋኖ ጋር ለመስራት ዝግጁ ነን ብሎ ሲናገር በብርሃን ፍጥነት ብቅ ብሎ የማረጋገጫውን ቃል አዎን ከህወሃት ጋር አብረን እንሰራለን የሚለውን ማረጋገጫ በአስረስ ማረ ዳምጤ አንደበት ሲነገር ለመስማት የበቃነው፡፡
💥 በዘመነ ካሴ የሚመራው የአማራ ፋኖ በጎጃም ከትህነግ ጋር ምን ሰጥቶ ምን በመቀበል ነው ምስጢራዊ ስምምነትን ለማድረግ የቻለው ??
ሁለቱ ቡድኖች ዝም ብሎ በነጻ አብሮ ለመስራት ተስማምተዋል ብሎ የሚያስብ አማራ ካለ ለአቅመ ፖለቲካ ያልደረሰ እንጭጭ ብቻ ሆኖ እናገኛለን፡፡ በፖለቲካው አለም ጥቅም አልባ ስምምነትና አጋርነት ፈጽሞ የለም፡፡ ምስጢራጺም ሆኑ ግልጽ ይፋዊ ስምምነቶች በሙሉ ሰጥቶ በመቀበል ላይ የተመሰረተ በመሆኑ ሁለቱ ፋሺስቶች ማለትም በዘመነ የሚመራው የሽፍታ ቡድን እና በዶ/ር ደብረጺዮን የሚመራው ትህነግ በኩል የተስማሙበት የሰጥቶ መቀበል ሁኔታ ምንድነው ብለን እንድንጠይቅ ያደርገናል፡፡ በዘመነ ካሴ የሚመራው ቡድን እራሱን በአማራ ስምና በአማራ ፋኖ ጎጃም ስም ሰይሞ ከህወሃት ጋር ሲደራደር ምን ለመስጠት ተስማምቶ ነው?? ከህወሃትስ ምን ለማግኘት ቃል ተገብቶለት ነው??
የወልቃይት ጠገዴ የራያ ጉዳይ የእኛ ችግር አይደለም በማለት ለሚታወቀው ዘመነ ካሴና ግብረ አበሮቹ ከህወሃት ጋር ለመስማማት በገጸ በረከትነት አሳልፎ የሰጠው የእነዚህኑን አማራዊያንን ማንነትና ግዛት ለትግራዩ ትህነግ አሳልፎ በመስጠት የተደረገ ስምምነት ሲሆን በትህነግ በኩል ወታደራዊ ትጥቅና ሎጀስቶክስ በምትኩ በማቅረብ ዘመነንና ቡድኑን የአማራ ክልል ገዢ የማድረግ የአቅም ግንባታ ለማቅረብ እንደተስማሙ ነው ከደረሰን ልዩ መረጃ ማወቅ የቻልነው፡፡ ሆኖም ይህንን ምስጢራዊ ስምምነቱን ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችል የመላው አማራ ፋኖ መሪነትን በእጁ ማስገባት ባለመቻሉ ክፉኛ ስጋትና ንዴት ላይ ያለው የዘመነ ካሴ ቡድን በዶ/ር ደብረጺዮን በኩል ከፋኖ ጋር ለመስራት ዝግጁ ነን የምትለዋን ቃል እንደሰማ በብርሃን ፍጥነት ብቅ ብሎ አዎን ከትህነግ ጋር አብረን ለመስራት ዝግጁ ነን በሚል ምላሽ ማረጋገጫ ለመስጠት እንደተገደደ ነው ማረጋገጥ የቻልነው፡፡
አንዳንድ የዋህ አማሮች፤ በተለይም ለህልውና ትግሉ ቀና አመለካከት ያላቸው አማሮች የአስረስ ማረ ዳምጤን ከህወሃት ጋር እንሰራለን ያለበትን ከአንከር ሚዱያ ጋር ያደረገውን ውይይት በአድናቆት ሲያስተጋቡት ታዝበናል፡፡ በመሰረቱ አስረስ ማረ ዳምጤ ከአንከሩ አዘጋጅ መሳይ መኮንን ጋር ባደርገው ቃለ ምልልስ የፖለቲካ ብስለቱን ያሳየበት ውይይት ሳይሆን ለጎጃም አማራ ያልገለጸውን ድብቅ የፖለቲካ ሴራን ያነገበ መርዘኛነቱን ያጋለጠበት ውይይት ሆኖ ነው ያየነው፡፡
የአንድ የበሰለ ፖለቲካ ፍልስፍናን አራማጅ ሰው ቀዳሚ ተግባር የሚሆነው ከማይጎራበተው እና አማራን በጠላትነት ከፈረጀ የጠላት ሀይል ጋር ተቀራርቦ ለመሰራት ያለውን ቁርጠኝነትን በመግለጽ ሳይሆን እታገልለታለሁ የሚለውን ህዝብ ጥቅምና ፍላጎትን በማስጠበቅ ደረጃ የማያወላውል ቁርጠኛ አቌምና አላማ እንዳለው በመግለጽ ነው መሆን ያለበት፡፡
አባቶቻችን ከእሩቅ ካለ መልዓክ ጎረቤትህ ያለው ሰይጣን ይቀርብሃል፤ ይጠቅምሀል ሲሉ ይደመጣሉ፡፡ ፈረንጆች ደግሞ ከማያውቁት መልዓክ የሚያውቁት ሰይጣን ይሻላል ሲሉ ይገልጻሉ፡፡ ዘመነ ካሴ፤ አስረስ ማረ ዳምጤ፤ ዝናቡ ልንገረውና መሰሎቹ ጎጃምና ወሎን ተሻግረው የአማራን ህዝብ በማንነቱ በጠላትነት ከፈረጀው የትግራዪ ትህነግ ጋር አብሮ ለመስራት የሚያበቃ ምስጢራዊ ስምምነት ከማድረግ ይልቅ በጎጃም ምድር ካለው አቻ ወንድማቸው የአማራ ፋኖ ህዝባዊ ድርጅት የጎጃም እዝ ጋር አብሮ ለመስራት የሚያስችል ስነልቦና እና አስተሳሰብ ይኖራቸው ይገባ ነበር፡፡
ድንበር ተሻግሮ ከአማራ ጠላት ጋር የሚደረግ ስምምነትና ግንኙነት ለአማራ ህዝብ ጥቅም ታስቦ ቢሆን ኖሮ ድንበር ተሻግሮ ከጠላት ጋር ለመስራት የቌመጠ አማራ ነኝ ባይ ቡድን በአብሮ አደጉ የአማራ ፋኖ ህዝባዊ ድርጅት የጎጃም እዝ አመራርና አባላት ላይ ጦርነት ባልከፈተ ነበር፡፡
ስለሆነም የዘመነ ካሴና የአስረስ ማረ ከህወሃት ጋር አብሮ ለመሰራት ዝግጁ ነን መግለጫ ያረጋገጠልን ምስጢራዊው ስምምነት በአማራ ህዝብ ዋጋ ከፋይነት በእኛ በአማራ ህዝብ ላይ የተፈጸመ ደባ መሆኑን ነው የሚያሳየን እንጂ ለአማራ ጥቅም ተብሎ የተደረገ ስምምነት አለመሆኑን ነው፡::
Comments