ሻ/ቃ ዳዊት ወ/ጊዮርጊስ |
በምናየው ታላቅ የፋኖ ትግል የዲያስፓራ ትልቁ ስራ ገንዘብ መስብስብ ነው:: እሱም እየቀዘቀዘ ሄዷል:: ጦርነቱን ያራዝምነው እኛው ነን:: ይህ ደግሞ ትልቁና ዋናው የጠላት ስትራተጂ ነው:: ጦርነቱን ማራዘምና ከአማራ ምድር እንዳይወጣ በማድረግ: ፋኖን በመከፋፈል አዳክመዋለሁ ! እበትነዋለሁ ! የሚል የአቢይ አህመድ ትልቁ የወቅቱ ስትራተጂ መሆኑን ተረድተናል::: በዚህም ምክንያት በአጠረ ጊዜ ሊጠናቀቅ የሚችለውን ትግል ዲያስፓራ በምቀኝነት: በቅናት: በሌለ ስልጣን ላይ በመፋተግ: በተቀጣሪነት: በጠባብ አስተሳስብ: ትግላችንን ወደኋላ በመጎተትና እንዲራዘም ብሎም እንዲዳከም በማድረግ ታሪካዊ ወንጀል እየስራ ነው::
ከዚህ መከፋፈል ነፃ ሆነን ፊትለፊት እየወረረ : እየገደለን: ያለውን የጋራ ጠላታችንን ልናሸንፈው የምንችለው በአንድነት ብቻ ነው::
አሸናፊነት ትብብርና የጋራ ስትራተጂ ይጠይቃል:: የተግባር ዲያስፓራ እንሁን:: አማራን እንደ ህዝብ ኢትዮጵያንም እንደ ሀገር ለማዳን ዋናው መሳሪያችን አንድነት ነው:: በውስጣችን ያለውን ልዩነት በመጠቀም አገራችንን ለማጥፋት: በአካባቢያችን ያለውን የሀይል አሰላለፍ ስንመለከት ፍፁም ፍፁም አደገኛ መሆኑን እንገነዘባለን::
በዲያስፓራ መጨቃጨቅና መዘላለፍ እንደ ባህልና እንደ ትልቅ የጦርነት ስትራተጂ ተደርጎ ተይዞአል:: ይህንን አይነት የጦርነት ስትራተጂ ከአማራ ዲያስፓራ ውጭ በታሪክም ባለንበት ጊዜም የትም አለም ተስምትም አያውቅም:: ለብዙዎች መዝናኛ: መሳቂያና መሳለቂያ ሆኗል:: አማራ ህልውናውን ለማስጠበቅ በፋኖ አማካኝነት በታላቅ መስዋዕትነት የሚደረገው የአማራ የህልውና ትግል ምን የፓለቲካ ፍልስፍና ያስፈልገዋል ? አላማችን ግልፅ ነው:: የፋኖ ሰራዊት ትግል ይህንን አላማ በሙያና በመሳሪያ ተደግፎ : ራሱ በመረጠው በመሰረቱት ከእሱ ጋር ተሰልፈው እዚህ ካደረሱት መሪዎቹ ጋር አዲስ አበባ ገብቶ ሁሉን አቃፌ የሆነ ጊዚያዊ መንግስት ማቋቋም ነው:: ይህ ነው ፍልስፍናው:: ስለ ጊዚያዊ መንግስትና አገራዊ መረጋጋት: ከዚያም በኋላ መፈፅም ስላለባቸው ሁሉ የፓለቲከኞች ሀላፊነት ነው:: እነሱ ስራቸውን ይጀምሩ:: የተጀመሩም አሉ:: በፋኖ ሰራዊት የህልውና ትግል ጣልቃ አንግባ::
ይህ ባለመሆኑ ምክንያት ከእውነተኛው አለም እርቀን የራሳችን የሆነ የማሸነፍ ሳይሆን በታኝ የሆነ አጥፊ ባህል እያስፋፋን ነው:: በዚህም ምክንያት በአገርም በውጭም ያሉ ጠላቶቻችን ወጥመድ ውስጥ አውቀንም ሳናውቅውም እየገባን ነው:: ይህንንም እውነታ ለመቀበል የብዙዎች አዕምሮ ተመርዟል:: ብዙ ጊዜ ጥቃት በተለይ የዘር ማጥፋት ወንጀሎች: ተጠቂ ህዝብን አንድ ያደርጋል:: ያሰባስበዋል:: የእነዚህ ወንጀሎች ሰለባ የሆነው ሀገር ቤት ያለው ህዝባችን አንድ ነው:: ድጋፍ ሊሰጠው የሚችለው ከአብራኩ የወጣው በዲያፓራ ያለው ብዙው የአማራ ህዝብ ግን አንድ አይደለም:: ይህ አንድ አለመሆን ዲያስፓራ አማራን ምን ነካህ ያስብለዋል? በህግም በሞራልም በእምነትም : ጠይቁ ራሳችሁን::
ከከፋፋይ አጀንዳ ለመራቅና በመሀከላችን ያሉ ጠላቶቻችንን ለይተን አውቀን አቸናፊ ሆነን እንድንወጣ አንድ እንሁን:: ትግላችን ከግለስቦች በላይ ነው:: የመሪ እጦት የለብንም:: ፋኖዎቻችችን ከምንገምተው በላይ ደረጃ በደረጃ እያደጉ በወታደራዊ ሙያዎችና በጠቅላላ የፖለትካ እውቀት መሪዎች እየወለዱ እዚህ አድርሰውናል:: እምነታችን በግለሰቦች ሳይሆን በፋኖ ላይ ብቻ ይሁን:: አማራ የተሸከመው ሀላፊነት የአማራን ህልውና ማስጠበቅ ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያም እንደ ሀገር እንድትቀጥል ነው:: የ120 ሚሊዮን ህዝብ ህልውና ከአማራ ህልውና ጋር የተያያዘ ነው:: የአማራ ህልውና የሚከበረው በተረጋጋች ኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ ነው:: ፓለቲከኞች ከጎን ሆናችሁ እርዱት::
ከላይ አትጫኑበት:: ይህንን ሳንገነዘብ የመከፋፈል አጀንዳችንን ብንቀጥልበት ለሚያስከትለው ውድቀት በመጀመሪያ ረድፍ ተጠያቂው የአማራ ዲያስፓራ ነው::
Comments