አለም አቀፍ የፋኖ ድጋፍ አስተባባሪ ኮሚቴ ነኝ የሚለው ቡድን ዓላማ ምንድነው ? በወንድወሰን ተክሉ

ይህ ምስል ጸሃፊውን አይወክልም!


«...አማራ ለ450 ዓመታ መንፈሱ የተሰበረ ገበሮ ሕዝብ ነው..» ሀብታሙ ተገኝ (ፕ/ር)

« እኔ እስክንድር  የአማራ ሕዝብ ከደረሰበት የህልውና አደጋ እኩል የሚሆን ዓላማ አለው ብዬ አላምንም» አቻምየለህ ታምሩ፤

አለም አቀፍ የፋኖ ድጋፍ አስተባባሪ ኮሚቴ ነኝ የሚለው ቡድን ዓላማ ምንድነው ?



በወንድወሰን ተክሉ

እራሱን አለም አቀፍ የፋኖ ድጋፍ አስተባባሪ ኮሚቴ ነኝ የሚለው ቡድን የዙም ውይይት ፕሮግራም ክፍል ሁለትን የተመለከተ ምልክታ:-

ባለፈው  ወር ብቻ ሳይሆን ባለፈው ዓመት ዴሴምበር 2023 ( ዛሬ ጃንዋሪ 1 ቀን 2024 ነን)  እራሱን አለም አቀፍ የፋኖ ድጋፍ አሰባሳቢ ኮሚቴ ብሎ የሚጠራው ቡድን «ጸረ አማራ ኢትዮጲያዊነት» በሚል አርእስት ስር ሀብታሙ ተገኝ (ፕ/ር) ዋና ተናጋሪ ተጋባዥ የሆነበትን  የዙም ውይይት አካሂዶ የነበረ ሲሆን የዚህ ውይይት ክፍል ሁለት  ባሳለፍነው ወር ዴሴምበር 23ቀን በማዘጋጀት አቻምየለህ ታምሩና ሀብታሙ ተገኝ (ፕ/ር) ተናጋሪ እንግዳ በማድረግ አካሂዷል። በእርግጥ  ከዚህ ከሁለተኛው የውይይት ፕሮግራም በፊት በተክሌ ይሻው በኩል የዙም ሊንክ ተልክሎኝ በሰዓት ጥበት ምክንያት መገኘት ባልችልም ዛሬ ግን በቻናላቸው ላይ የጫኑትን ይህን ክፍል ሁለት ውይይት ከተመለከትኩ በኋላ ይህን ምልክታዬን  አንባቢው ሊረዳ በሚያስችል መልኩ አንድ ሰዓት ከሰላሳ ደቂቃ የፈጀን ውይይት ይዘት በመጭመቅ እንደሚከተለው አቅርቤያለሁ።


ይህ ምስል ጸሃፊውን አይወክልም!



1ኛ - ውይይቱን አዘጋጅን ማንነት በተመለከተ፦  አለም አቀፍ የፋኖ ድጋፍ አስተባባሪ ኮሚቴ ባለፈው መስከረም ወር ላይ  በጌታቸው በየነ ሰብሳቢነት ተመሰረትኩ ብሎ እራሱን ያስተዋወቀ ሲሆን ጌታቸው በየነ ማለት ደግሞ በወቅቱ የ I AM ሰብሳቢ የነበረ እና እንዲሁም  በታላቁ እስክንድር ነጋ  ባለፈው ግንቦት 12 ቀን 2015 የተመሰረተው የአማራ ፋኖ ሕዝባዊ ግንባር ምስረታ ማግስት ግንባሩን በመቃወም ከተነሳ በሃላ በሀገር ውስጥ ያሉትን ፋኖዎቻችን በሚከፋፍል ሁኔታ  ከሕዝባዊ ግንባሩ ጋር አትሰለፉ አንድነት አትፈጠሩ የሚል ችግር መፍጠሪያን ተግባር ላይ በመሰማራት መስከረም ላይ ይህንን ኮሚቴ ሊያቌቌም መቻሉ ይታወቃል።

ዛሬ በዚህ ድርጅት ስም እየተካሄደ ያለውን የዙም ውይይት በማዘጋጀት ደረጃ እነ ተክሌ ይሻው ሀብታሙ ተገኝ (ፕ/ር) ያዘጋጁት ውይይት ሲሆን የዚህ የዙም ውይይት ዓላማ እንደዚህ ጸሓፊ አረዳድና እይታ ያለውን ወደ ኋላ አቆይቼ በአዘጋጆቹ በኩል የተገለጸው ለአማራ ሕዝብ የህልውና ትግል መሪን ማውጣት የሚል ዓይነት ይመስላል።

2ኛ - 1:30 ደቂቃ የፈጀው ክፍል ሁለት ውይይት ፕሮግራም ይዘት

ሀብታሙ ተገኝ (ፕ/ር) እና አቻምየለህ ታምሩ ዋና እና ብቸኛ ተናጋሪ የሆኑበት እና አንድ ሰዓት ከሰላሳ ደቁቃ የፈጀን  ክፍል ሁለት ውይይት በሁለት ክፍል ተክፍሎ የሚታይ ሲሆን ከፕሮግራሙ መጀመሪያ እስከ 50ኛው ደቂቃ ያህል ያለው ክፍል  በአጠቃላይ የአማራ ሕዝብ ሁኔታ በደርግና በንጉሳዊው ስርዓት ዘመን የነበረበትን  ታሪካዊ ሁኔታ ላይ ያተኮረ ሲሆን ከ50ኛው ደቂቃ በኋላ ባለው ክፍል ለተኛው የውይይቱን ክፍል ጥያቄና መልስ መልክ የተካሄደ ፕሮግራም ነው።

ታሪካዊ ዳራዎች ላይ ያተኮረውን የውይይት ክፍል በተመለከተ፦

ሁለቱ ተናጋሪዎች ሀምሳውን ደቂቃ የፈጁት ከዘውዳዊው ስርዓት ጀምሮ በአብዮቱ ዘመን ስለተፈጠሩት እንደነ ኢሕአፓ፣ደርግ፣ኦነግና መሰል አደረጃጀቶችን ታሪክ በመጥቀስ በመሬት ላራሹ በ1960ዎቹ ተማሪዎች አመጽና አቢዮት፣በኢሕ አፓ፣መኢሶን፣በደርግ እና መሰል ሀይሎች አማራው ቀዳሚ ኢላማ ተድርጎ የተጨፈጨፈበትን ሂደት በመግለጽ  አቢዮቱ ጸረ አማራ መሆኑን እና የዚህ አቢዮት ባለቤት የሚባሉት እንደነ ኢሕአፓ፣ መኢሶን እና ደርግን ጨምሮ በዘመኑ የነበሩ ድርጅቶች በሙሉ ጸረ አማራ መሆናቸውና መጨረሻም አሸናፊ ሆኖ የአቢዮቱ ባለቤት የሆነው ደርግ ጸረ አማራ ብቻ ሳይሆን የኦሮሞ ሀይል መሆኑን በመግለጽ ላይ ያተኮረ ታሪክ ተኮር  ይዘት ያለው ነው ያቀረቡት።  ይህንን ታሪክ ተኮር ታሪክን ያቀረቡት ጸረ አማራ ዘመቻ የዛሬ ክስተት ብቻ ያለመሆኑን እና 50 እና 60 ዓመታት ያለው መሆኑን በመግለጽ  የዛሬው የህልውና አደጋ ስር የሰደደ መሆኑን ለማሳየት ነው ብዬ በቅንነት እንዳልቀበል ያደረገን በክፍል ሁለት ላይ ሲጠቀሙበት አይቻለሁ።

በዚህ ክፍል አንድ ታሪካዊ ዳራ ጉዳይ ላይ ያሉኝን በርካታ ጥያቄና ምልክታን ወደ ጎን እስቀምጬ ( በዚህ ሰዓት ለእኔ ያ የትናንትና ታሪክ አማራ ሆኜ ከአማራ ጋር በመከራከር ግዜዬን ማቃጠል አለብኝ ብዬ ስለማላምን አልፌዋለሁ)  ወደ ሁለተኛው እና ለዚህ ጽሁፍ ዋና ምክንያት ስለሆነው  የውይይት ክፍል ልውሰዳችሁ።

በጥያቄና መልስ ላይ ባተኮረው የውይይቱ ክፍል ሁለት - ጠያቂው አራት ግዜ የጠየቀውና በይዘቱ ግን አንድ አይነት ጥያቄ በታላቁ እስክንድር ነጋ የሚመራው የአማራ ፋኖ ሕዝባዊ ሰራዊት እና በተለይ በተለይ  ታላቁ እስክንድር ነጋን እና ሻ/ ዳዊት ወልደጊዮርጊስን ብቻ የተመለከተ ጥያቄና ምላሻቸውን በተመለከተ፦

እዚህጋ አንባቢው ሁለቱ ተናጋሪዎች ሀብታሙ ተገኝ (ፕ/ር) እና  አቻምየለህ ታምሩ በክፍል አንድ ታሪካዊ ዳራ የውይይት ፕራግራም ላይ  በስፋት አጽንኦት ሰጥተው ሲገልጹ በነበረው ከ1960ዎቹ ተማሪዎች አመጽ ጀምሮ የተፈጠሩት ድርጅቶች፣መንግስት መሆን የቻሉና ያልቻሉ ተቃዋሚዎች በሙሉ፦

1ኛ- ጸረ አማሮች መሆናቸውን እና አማራውን እየለዩ ለስልጣን እንዳይበቃ በማድረግ ከሀብት በማገድ መስራታቸውን እና፤

2ኛ- እነዚህ ሀይሎች ደርግ የኦሮሞ አቢዮት መሆኑን እና የተቀረው ተቃዋሚ ወያኔና ሻእቢያ መሆናቸውን በመግለጽ ከ1966  እስከ 2023 ድረስ ያለው ስርዓተ መንግስትና አደረጃጀቶች በሙሉ ጸረ አማራ ሀይሎች ናቸው በማለት የገለጹትን 50 ደቂቃ የፈጀን ንግግራቸውን ተከትሎ የቀረበላቸው ጥያቄ ታላቁ እስክንድር እና ሻ/ ዳዊት የዚህ የጸረ አማራ ትውልድ ከሆነው ከትናትናው ጸረ አማራ ሀይል አካልና አባል ሆነው ሳለ የአማራን ሕዝብ የህልውናን ትግል እንዴት መምራት ይቻላሉ የሚል አይነት ጥያቄ ነው ቀረበላችሁ ተብለው ሲመልሱ የሰማሁት።

ሀብታሙ ተገኝ (ፕ/ር) እና አቻምየለህ ታምሩ  የአማራን ሕዝብ የህልውናን ትግል ታግሎ በማታገል ላይ ስላለው ታላቁ እስክንድር ነጋ እና ሻ/ ዳዊት ወልደጊዮርጊስ ከተናገሩት ውስጥ ጥቂት ያህሉን ላስቀምጥላችሁ፦

አቻምየለህ ታምሩ ስለ ታላቁ እስክንድርና ሻ/ ዳዊት ከሰጠው ምላሽ ተጨምቆ በጥቂቱ፦

እኔ እስክንድር የአማራ ሕዝብ ከደረሰበት የህልውና አደጋ እኩል የሚሆን ዓላማ አለው ብዬ አላምንም...❗



... አንደኛ -  አሁን አማራ ትግል ውስጥ  የእዚህ የዚያ እየተባሉ በብዛት  የምናያቸው ሰዎች አንድም በባለፈው ዘመን በነበራቸው ተሳትፎ ዛሬ አማራው ከሚታገላቸው ሰዎች የማይተናነስ ጉዳት  ያደረሱ ለዚያም አውቀው ይቅርታ ያልጠየቁ  በዚያም ጭንቅላት እስከዛሬ ድረስ ሚመሩ መሆናቸውና ....

... ሁለተኛ ለአማራ የያዙትን አላማ የማናውቃቸው  አሁን ለምሳሌ እስክንድር የያዘው ዓላማ ምንድነው ተብለን ብንጠየቅ ብዙዎቻችን መልስ የለንም.....ምን ዓላማ አለው እስክንድር ለአማራ ?

... ብዙ ሰው ብላንክ ቼክ  ይሰጣል።

የአማራ ሕዝብ የሚታገልለትን ዓላማ ሳይዙ የአማራ ትግል መሪ ነን ለሚሉ አማራው ዝም ብሎ ብላንክ ቼክ መስጠት የለበትም።

... ትናንትና አማራን ሲያጠፉ የነበሩ - ዛሬ ላይ መጥተው መሪ ነን ይላሉ።

( አቻምየለህ ለተናገራቸው ቃላቶች ማፋላሻን ማቅረብ ብችልም ለአንባቢ መተውን መርጫለሁ። አንባቢ እራሱ መዝኖ በአመክኒዮ እንዲመለከተው አልፌዋለሁ)

 ሀብታሙ ተገኝ (ፕ/ር) ምላሽ በጥቂቱ ተጨምቆ፦

...ማንነታቸውን የማናውቅ እየደገፍን  ለስልጣን በማብቃት የከፈልነውን ዋጋ አይተናል...

... እኔ ለእስክንድር ታላቅ ክብር አለኝ፡ ለሻ/ ዳዊትም ክብር አለኝ። እስክንድርን መተቸት ይከብደኛል፣...የምናከብራቸውን ለመተቸት እንቸገራለን... 

...ግን ባለመተቸታችን ብቻ 

...ስንኖር  ኢትዮጲያዊ ስንሞት ኢትዮጲያ ያለንን አቢይን አምነን ምን እንዳደረገን እናውቃለን 

... ከእንግዲህ ወዲያ አማራ ሆኖ  አንዱንም ፖለቲከኛን የሚያምን ካለ  ችግር ያለበት አማራ ነው። ማንንም ማመን አይገባንም።

... አማራ ለ450 ዓመት መንፈሱ የተሰበረ ገባሮ የሆነ ሕዝብ ነው...  መንፈሱ የተሰበረ ሕዝብና ትውልድ ይዘን የትም አንደርስም...

 ... መንፈሱ የተሰበረን አማራ ትከሻችን ላይ ተሸክመን መጋዝ የለብንም። 

 ...የአማራው ቆሻሻ  ብዙ ነው። በጣም ብዙ ቆሻሻ ያለን ሕዝብ ነን......



የተናጋሪዎቹ ማንነት፦

 ሀብታሙ ተገኝ (ፕ/ር) እና አቻምየለህ ታምሩን ሁላችሁም ታውቌችኋላችሁ። ሀብታሙ ተገኝ በረራን መጽሀፍ ጽፎልናል ( ከመጽሀፉ ይዘት ላይ ቅንጣት ችግር የለብኝም። የዳዊት ከተማ የሆነቺውን የዛሬይቱን አዲስ አበባን ባለቤትነትን በማስረጃ አስደግፎ ያቀረበ ማለፊያ መጽሓፍ ነው) ሆኖም በዚህ የህልውና ትግል ላይ ከምን አንጻር እንደሆነ ጉዳዩን ለባለቤቱ በመተው ከእነ ጌታቸው በየነ፣ ወሰን ይጥና፣ ተክሌ ይሻውና መሰል በጣት የሚቆጠሩ ጋር በመሆን  በአለም አቀፍ የፋኖ ድጋፍ አስተባባሪ ኮሚቴ ስር ሆኖ በታላቁ እስክንድር ነጋ እና በሻ/ ዳዊት ወልደጊዮርጊስ ላይ ተከታታይ የሆነ ዘመቻን እያሳለጠ ያለ ፊት መሪ ነው።

ሁለተኛው ተናጋሪ አቻምየለህ ታምሩ ( በጣም በተባ ብእሮች በተለይም በታሪክ ነክ ይዘት ባላቸው አር እስቶች ላይ በሚጽፋቸው የማደንቀው)  በአማራ ጉዳይ ላይ ብቻውንና ነጠል ብሎ በመጻፍ የምናውቀው ወንድም ሲሆን ዛሬ በእነ ጌታቸው በየነ መሪነት ተቌቌመ በሚባለው አለም አቀፍ የፋኖ ድጋፍ አስተባባሪ  ኮሚቴ ተጋብዞ የተሳተፈ ነው። አቻምየለህ ታምሩ ከሚታወቅበት የተባ ብእሩ ጎን ለጎን አንድ በዚህ በአማራ አደረጃጀት ውስጥ ባለን ሰዎች ዘንድ የሚታወቅበት ለየት ያለ ጉዳይ ቢኖር ለአማራ ሕዝብ የህልውና ትግልም ይሁን ለሰብዓዊ እርዳታ ድጋፍ ማሰባሰቢያ ዝግጅት ላይ ቢጋበዝ ለመገኘት ፈጽሞ ፈቃደኛ ያለመሆኑ ጉዳይ ነው። (  በግሌ  በአለን እና በጋሻ አማራ ባዘጋጀናቸው የድጋፍ ማሰባሰቢያ ዝግጅቶች እና ባዘጋጀነው ሕዝባዊ ውይይት ላይ በእንግድነት ጋብዘን ያረጋገጥኩት ነው)  በተጨማሪም አቻምየለህ ታምሩ ትናንትን መሰረት አድርገን ነው ዛሬን  የምንወስነው በሚለው ፍልስፍናው ከ2023  እስከ 1950ዎቹ እና 1960ዎቹ ድረስ ወደ ኋላ በመጔዝ በዛሬ ታጋዮች ላይ የሰላ ተቌውሞና ትችት ያቀረበ ሰው እንደመሆኑ መጠን በታሪክ የብዓዴን አባል እንደነበረ መግለጹ ተገቢ ይመስለኛል።

አጠቃላይ የአለም አቀፉ የፋኖ ድጋፍ አሰባሳቢ ኮሚቴ አላማ እና የሁለቱ ተናጋሪዎች ምላሽ አቅጣጫ የሚያሳየን ምንድነው?? 

በሁለት ክፍል የተከፈለውን የውይይታቸውን ይዘት ስንመለከት፦

1ኛ -ታሪክን መሰረት በማድረግ የአማራን ጠላቶች በማሳየት ያንን ታሪካዊ የአማራ ጠላት የሆነን ሀይል ከዛሬዎቹ ታጋዮቻችን በተለይም ከታላቁ እስክንድር ነጋና ከሻ/ ዳዊት ወልደጊዮርጊስ ጋር በማያያዝ የአማራ ፋኖ ሕዝባዊ ሰራዊት እና አመራሩ የትግሉ መሪም ሆነ አመራር መሆን የማይገባቸው ናቸው የሚልን መልእክት ማሰራጩት፤

2ኛ-  የአማራ ሕዝብ በታጋዮቹ ሁሉ እምነት እንዳይጥልና  የሚታመን ሰውና የሚታመን መሪ ታግሎ አታጋይ ድርጅትም ሆነ አመራር የለም በሚል እምነት ተስፋ ቆርጦ የሚይዝ የሚጨብጠውን እንዲያጣ ማድረግ

3ኛ- በታላቁ እስክንድር ነጋ የተመሰረተውን አታጋይ ድርጅትን፦

1ኛ- ድርጅቱ የሚመራው በሻ/ ዳዊት መሆኑን በማሳየት ትግሉን እየመራ ያለው ለአማራ ሕዝብ የህልውና ትግል ዓላማ የሌለው የትናትና ጸረ አማራ የሆነ ሀይል ነው የሚልን መሰረተ ቢስ ንክኪነትን ፈጥሮ ማሳየት፤

2ኛ- በአማራ ፋኖ ሕዝባዊ ሰራዊት ድርጅት እና ድርጅቱ ዓለም አቀፍ የድጋፍ አሰባሳቢ ኮሚቴ አድርጎ ባቌቌመው በሻ/ ዳዊት ከሚመራው ኮሚቴ ጋር ያለውን የስራ ክፍፍል  እና የተለያየ የኋላፊነት ስራን እንደሌለ አድርጎ በማቅረብ የፈጠራን ብዥታና ስም የማጠልሸት ስራን መስራት፤

4ኛ - ታላቁ እስክንድር ነጋን የትናትና ስርዓት የደርግና የወያኔ(ኢሕአዴግ) ዘመን የጸረ አማራ ሀይሎችና አደረጃጀቶች አካል አድርጎ በማቅረብ ለአማራ ሕዝብ የህልውና ትግል ዓላማ የሌለው The wrong person at the Right place አድርጎ በመሳል ቅቡልነቱን መሸርሸርና ብሎም ከተቻላቸው መናድ፤

5ኛ - ታላቁ እስክንድር ነጋ ያለውን  ቅቡልነት  ሕዝቡ ዝም ብሎ ከመሬት ተነስቶ ልክ Blank Check እንደሚሰጥ በነጻ የተሰጠው ምንም ያልሰራና ምንም ሊሰራ የማይችል ብሎ በመግለጽ መሪ የለንምን ሀሳብ ገዢ ሀሳብ የማድረግን ስራ በዘመቻ መልክ እየሰሩ መሆናቸውን በትንሹ መግለጽ ይቻላል።

የሁለቱ ተናጋሪዎች እና ብሎም ውይይቱን አዘጋጅ የሚባለው አለም አቀፍ የፋኖ ድጋፍ አሰተባባሪ ኮሚቴ የፈጸማቸውና እየፈጸማቸው ያሉ ወሳኝ የሆነ የውሸት መሰረተ ቢስ የፈጠራ ቅጥፈቶች፦

1ኛ- የአማራ ፋኖ ሕዝባዊ ሰራዊት እና በድርጅቱ የውጭ ድጋፍ አሰባሳቢ ኮሚቴ (በሻ/ ዳዊት ሰብሳቢነት በሚመራው ማለቴ ነው) መካከል ያለውን የተለያየ የስራ ክፍፍልና ኋላፊነትን እያውቁ ሆን ብለው በመደበቅ ሻ/ ዳዊትን የድርጅቱ የፖለቲካ ውሳኔዎችን ወሳኝ ፖሊሲ አውጪና ብሎም መሪ አድርጎ ማቅረብ። ( ይህንን ጉዳይ በተመለከተ ሻለቃው ባለፈው ሳምንት ከ360 ሚዱያው ጋዜጠኛ አፈወርቅ አግደው ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ተጠይቀው የሰጡትን ምላሽ አንባቢ ሄዶ ማደመጥ ቢችልም እሳቸው ያሉት «እኛ በውጪ ያለን ድጋፍ ከማሰባሰብ ውጪ ምንም ተሳትፎም ሆነ ሚና የለንም። ድርጅቱ በሚሰጠን አቅጣጫና ትእዛዝ ብቻ የምንሰራ ነን » በማለት በሀገር ውስጥ እና በውጭ ባለው መካከል ያለውን የስራና የሀላፊነት ልዩነትን አስቀምጠዋል)  በተለይ በተለይ እንደ ሀብታሙ ተገኝ (ፕ/ር) እና አቻምየለህ አይነት ስለ አደረጃጀት እናውቃለን ባይ አንደበት የዚህ ድርጅታዊ አሰራር እየታወቀ ሆን ብሎ በተራ ፈጠራና ቅጥፈት ሲስተጋባ ማየት በጣም ያሳፍራል።

2ኛ - ታሪክ እናውቃለን ባዬቹ ሁለቱ ተናጋሪዎች የእስክንድርን ህይወት ከአማራ ሕዝብ ትግል አንጻር ቅንጣት የማያውቁ መሀይማን መሆናቸውን እና ወይም እያወቁ ሆን ብለው በማፈን  በፈጠራ ቅጥፈት የገለጹበት አገላለጽ። ( እዚህ ላይ 100% እርግጠኛ ሆኜ የምገልጸው እስክንድር አማራነቱን በይፋ አደባባይ ገልጾ ለአማራ ሕዝብ ድምጽ በሚሆንበት ዘመን ሀብታሙም ሆነ አቻምየለህ ወይም ተክሌ ይሻው አማራ ነኝ የማይሉ ሰዎች መሆናቸውን ነው። በአማራ ትግል ታሪክ ውስጥ ዘመን ተሻጋሪ ከሆኑት መፈክሮች ውስጥ አንዱ የሆነው አማራ ታሪኩን ያድሳል መፈክር በ1985 ጀምሮ እስክንድር በሚያሳትማቸው ጋዜጦችና መጽሔቶች ሁሉ መፈክሩ አድርጎ የሚሰራበት ነው። እንግዲህ ሀብታሙና አቻምየለህ ይህንን ሰው ነው ለአማራ ያለውን ዓላማ አናውቅም የሚሉት)

3ኛ- ፕሮግራሙ ውይይት ነው የሚል ይሁን እንጂ ውይይት ሳይሆን የአንድ ወገን አንድን የአማራን ታጋይ ልጅና ታጋይ ድርጅት ላይ ያነጣጠረ ጸረ ትግል የፕሮፖጋንዳ መድረክ ነው እንጂ ተናጋሪዎች ከሚያስተጋቡት ግልብ የጥላቻን ሀሳብ የሚሞግት የተለየ ሀሳብ የማያስተናግዱበት መሆኑ ነው።

4ኛ - የውይይቱን መሪ ቃል ...  መጠየቅ .. ያልጠየቀ ትውልድ ይጠፋል የሚል አድርገው እና ተናጋሪዎቹም እኛ ለአማራ እንታገላለን የሚልን ሁሉ እንጠይቃለን መጠየቅም አለብን እያሉ በተግባር ሲያስተጋቡ የተደመጡት ጥያቄ ሳይሆን ደምድሞ ወስኖ መፈረጅን ሲሆን ከሁሉም በላይ ደግሞ ሕዝቡ ለታላቁ እስክንድር ነጋ በነጻ የሰጠውን ቅቡልነትን ነጥቆ ይውሰድ ሲሉ በአማራጭ  የመሪነቱን ቅቡልነት ከእስክንድር ነጥቃችሁ ለእከሌ ለሚባል ድርጅትና መሪ ስጡ ትግሉን መሪ አልባ ለማድረግ መለፈፋቸው ነው።

መደምደሚያ ፡-

 መታመሜን ገልጾ መፈወሻ መድሃኒትን ሊያዝልኝ ያልቻለን ሰው የሕክምና ባለሙያ ሳይሆን የምለው  በጤናማነቴ ቀንቶ ታመሀል ያለኝ ተራ ምቀኛ ብዬ ነው የምገልጸው❗

አለም አቀፍ የፋኖ ድጋፍ አስተባባሪ ኮሚቴ ባዘጋጀው ክፍል አንድ እና ክፍል ሁሉት ሰፊ ውይይት ትክክልም የሆኑም ሆነ ትክክል ያልሆኑ ችግሮች፣ተጋዳሮቶች በገፍ ተዥጎድጉደዋል። የሁለቱም ክፍል ፕሮግራም በሚያስብል ደረጃ ከ90% በላይ የሆነው የውይይቱ ይዘት ከጥንት ታሪካዊ ክስተት እስከ አሁናዊ ኩነት የተፈጠሩ ችግሮች በ360 አንግል ቅኝት አንጻር እየተቃኙ በገፍ ሲዘረገፉ ማርከሻ መድሃኒታቸውን እና አማራጭ ምትኮችን ቅንጣት ባለማቅረብ የተደመደመ ነው።

የተገለጹትን ችግሮች ተግዳሮቶችን አደጋዎችንና መሰል እንቅፋቶችን የተጋነኑ አሊያም የተፈበረኩም ሆነ በትክክል የተፈጠሩ እንኴን ቢሆኑ ችግሮችን ብቻ ማወቅም ሆነ ማሳየት ምሉእ አድርጎ አቸው ላለንበት የህልውና ትግል መፍትሄ አይሆኑም። እጅግ ቢበዛ ግማሽ መፍትሄ ናቸው።

ዛሬ እኛ በከባድ ፍልሚያ ላይ ያለን ሕዝብ ነን። ፍልሚያው የመሞትና የመኖር ያህል እጅግ ወሳኝ የሆነ ፍልሚያ ላይ ነው ያለነው። 

በዚህ ሰዓት  የተባበረ ሁለንተናዊ አንድነት ከመቼውም ግዜ በላይ የምንፈልግበትና የሚያስፈልገን ወቅት ነው። ያለን የሰው ሀይል፣ የፋይናንስና የሎጀስቲክስ አቅርቦት በእንድ አቅጣጫ ወደ ትግሉ እንዲያመራ በእጅጉ የምንሻበት ወቅት ላይ እንገኛለን።

ፊደል ቆጥሮ ፕ/ር ነኝ የሚለን ሀብታሙ ተገኝም ሆነ በታሪክ ጠብሰቅ ያለ እውቀት ያለኝ ነኝ የሚለን አቻምየለህ ታምሩ እና እነሱን ያሰባሰባው ድርጅት ተብዬ  ለፋኖ በፋኖ ስም የተሰባሰብኩ አለም አቀፍ የፋኖ ድጋፍ አስተባባሪ ነኝ ብሎ እራሱን ሲገልጽ የምንሰማው ቡድን እጅግ ያስጨነቃቸው ማን መሪ ይሁን (ያውም ዳያስፖራ ተጎልተው) የሚለው ጉንጭ አልፋ ፍሬከርስኪ ጉዳይ ነው እንጂ የጠላትን ወረራ መክቶ አክሽፎ ከማክሰምና ከመደምሰስ አንጻር ከእኛ የሚጠበቀውን አቅርቦት ለማቅረብ እንረባረብ ብለው ሲያስቡ አለማየት ያስፍራል።

እጅግ ያስደነቀኝ ሁለቱም ተናጋሪዎች ማራቶን ከሆነው ችግሮችን ብቻ ከገለጸው ንግግራቸው በሃላ መፍትሔ ብለው በአጭሩ ሲገልጹ የእስክንድርን ቅቡልነት መልሳችሁ ንጠቁ ከሚል ጎን ለጎን  ቅቡልነቱን ለእከሌ ስጡ ያለማለታቸውና በተለይም ሀብታሙ ተገኝ (ፕ/ር) አማራ አንድንም ሰው የሚያምን ከሆነ አእምሮው ጤናማ ነው ብዬ አላምንም ብሎ እርሰበርስ እንዳንተማመን ያስቀመጠውን መፍትሔ ልክ አንድን መርዝ መድሃኒት ነው ብሎ ከሚሰጥ ጠላት ለይቼ ላየው እለመቻሌ ነው።

«....አማራ እጅግ ቆሻሻ ሕዝብ ነው። አማራ ለ450 ዓመታት መንፈሱ ተስብሮ ያለ ገባሮ ሕዝብ ነው። መንፈሱ የተሰበረን ሕዝብ ይዘህ የትም አትደርስም ...» ብሎ የተናገረው እንግዲህ ፕ/ር ነኝ ነው ባዩ ሀብታሙ ተገኝ ነው።

ይህ ማለት አማራው ለ450 ዓመታት በባርነት የኖረ ሕዝብ ነው ሲል በግብጽ በባርነት 400 ዓመታት ከቆዩት እስራ ኤላዊያን ሪኮርዱን በነጠቀ በባርነት ስር ያለ ሕዝብ ማለት ነው። ገባሮ ማለት ኦሮሞው በ16ኛው ክፍለ ዘመን በባሌ መዳ ወላቡ በሚባል ውሱን አካባቢ ተወስኖ ሲኖር ከነበረበት ስፍራ በወረራ እየተስፋፋ በያዛቸው አካባቢዎች ያሉትን ሕዝብ እያስገበረ የተስፋፋበትን ሁኔታ የሚገልጽ ሲሆን እንደ ሀብታሙ ተገኝ አገላለጽ አማራ ለ450 ዓመታት ያህል በኦሮሞ እየተገዛ ያለ መንፈሱ የተሰበረ ገባሮ ነው እያለን ነው።

እናም እነዚህን ተከታታይ የውይይት ፕሮግራም ይዘት ስንመለከት የአለም አቀፍ የፋኖ ድጋፍ አስተባባሪ ኮሚቴ ነኝ የሚለን ቡድን እንቅልፍ አጥቶ ሌት ተቀን የሚሰራው ጸረ እስክንድር እና ጸረ ሻለቃ መሰረተ ቢስ የፈጠራ ፕሮፖጋንዳን እየሰራጨ ያለ ብቻ ሳይሆን በአጠቃላይ እንደ አማራ መሪ አልባ መንፈሱ የተሰበረ ትውልድ ሊያደርግ የሚቃትት መሆኑን ነው። አንላቀቅም። ለጊዜው አበቃሁ።




0 Comments