Skip to main content

ኢትዮጵያ አትፈርስም እያሉ በተጨባጭ ግን እያፈረሷት ነው፤ በዶ/ር ሽፈራዉ ገሰሰ


ምስሉ ጸሃፊውን አይወክልም!

ኢትዮጵያ ማለት አገር ናት፣ አንድ አገር ደግሞ አገር ለመባል መሬቱ፣ ጫካው፣ ወንዙ፣ ሸንተረሩ፣ ባህሩ፣ ሀይቁ፣ ተራራው፣ ሜዳው፣ደጋው፣ ቆላው፣ ወይናደጋው፣ በረሀው በጠቅላላው መልክዓምድሩ ብቻ ሳይሆን ሌሎች ብዙ ነገሮችን ያጠቃልላል። አገር ሲባል መሬቱ፣ ውሃ ሀብቱ፣ አየሩ፣ ሉዓላዊነቱ ብቻ ሳይሆን ዋነኛው በውስጡ የሚኖረው የአገሪቱ ባለቤት የሆነው ህዝብ ባህሉ፣ ቋንቋው፣ ወጉ፣ ልማዱ፣ ሃይማኖቱ፣ታሪኩ፣ ሰንደቅ አላማው፣ ብሔራዊ መዝሙሩ፣ መለያ አርማው፣ስርዓተ መንግሥቱ፣ አንድነቱ ስርዓተ ትምህርቱ፣ ስነ ጥበቡ፣ ስነ ህንፃው፣ ታሪካዊ ቅርሶቹ፣ ማህበራዊ መስተጋብሩ፣ ብሔራዊ በዓላቱ፣ ጀግኖቹ፣ የጦር ድሎቹ፣ የነፃነትተጋድሎ ታሪኩ፣ ምግብና የምግብ ስርዓቱ፣ኢኮኖሚው ወዘተ የሚያጠቃልል ነው።

ኢትዮጵያ የብዙ ሺህ አመታት ስርዓተ መንግሥት ያላት፣ በቅኝ ያልተገዛች ከዓለማችን ቀደምት ስልጣኔወች ካላቸው ጥቂት አገሮች ውስጥ አንዷ ስትሆን በአሁኑ ወቅት ግን ከፍተኛ አደጋ ውስጥ ትገኛለች። ጠቅላይ ሚኒስቴሩን ጨምሮ ሌት ከቀን በሚዲያ እየወጡ ኢትዮጵያ አትፈርስም እያሉ እየለፈፉ በተቃራኒው ግን አገሪቱን እንመራለን ብለው የተሰየሙ ባለስልጣኖች፣ የእነርሱ አላማ ተባባሪ የሆኑ የፓለቲካ ድርጅቶችና ሌሎች አደረጃጀቶች በጋራ በመሆን በተጨባጭ ኢትዮጵያን እያፈረሷት ይገኛሉ።

እየሆነ ያለውን ከላይ ከዘረዘርኳቸው የአገር ምልክቶች ውስጥ ጥቂቶቹን ወስጀ ለማሳየት እሞክራለሁ።

ሉዓላዊነት

አንድ ሉዓላዊ ወይም ነፃ የሆነ አገር የራሱ የሆነ በዓለም አቀፍ ህግ የታወቀ የየብስ የባህርና የአየር ክልል አለው። ይህ አገር ከሚሰጠው ፈቃድ በስተቀር በማንኛውም አገር ወይም አገሮች ሊደፈር ወይም ሊጣስ አይችልም። ነገር ግን በአሁኑ ሰዓት የኢትዮጵያ ሉዓላዊነት በሰሜን ምዕራብ በሱዳን ጦር በደቡብ ምዕራብ በደቡብ ሱዳን አማፂ ኃይሎች ተደፍሮ ብዙ ኪሎሜትሮች አልፈው እርሻ እያረሱና ማዕድን እያወጡ ሲሆኑ የአገሩ ባለቤት የሆኑት ኢትዮጵያውያን ግን ንብረታቸው ተዘርፎ ህይወታቸውን ለማትረፍ ተፈናቅለው በየቦታው ተበትነው የስቃይ ህይወት እየገፉ ይገኛሉ። ይህ እየሆነ እስካሁን ድረስ ኢትዮጵያን እያሰተዳደርሁ ነው የሚለው መንግሥት ምንም እርምጃ አልወሰደም። የአገሪቱ ሉዓላዊነት መደፈርም ሆነ ከነዚህ አካባቢውች የተፈናቀለው ህዝብ ስቃይ ፈፅሞ ሲያሳስበው አልታየም። ሉዓላዊነቱ ረዘም ላለ ጊዜ ያልተከበረ አገር በመፍረስ ላይ ያለ አገር ተብሎ የሚቆጠርበት ዕድሉ ሰፊ ነው።

ስርዓተ መንግሥት

መለስ ዜናዊ በኢትዮጵያና በአማራው ህዝብ ላይ ከነበረውየመረረ ጥላቻ የተነሳና ከፋፍሎ ለመግዛት እንዲያመቸው በየትም አገር ህገ መንግሥት የማይገኝ የኢትዮጵያን ህዝብ በጨቋኝና ተጨቋኝ በመከፋፍል ተጨቋኝ ነበሩ የተባሉት ጨቋኝ ነበር በተባለው ህዝብ ላይ የማያባራ የዘር ማጥፋትወንጀል እንዲፈፅሙበት ህጋዊ ፈቃድ ሰጥቶ እስከ አሁን ድረስ ተለይቶ እየተጨፈጨፈ ይገኛል። ይህ አየተጨፈጨፈ ያለ ህዝብ ለነፃነቱና መብቱ በሙሉ አቅሙ መነሳቱ የማይቀር መሆኑን አስቀድሞ በመገንዘብ የመፍትሄ እርምጃ ሲወሰድ አይታይም። እንዲያውም ይባስ ብሎ መንግሥት ጨፍጫፊዎችን በግልፅ እያገዘ ስምሪት እየሰጠ ይገኛል። ታዲያ ይህ ሁኔታ እንዴት አገርን አፅንቶ ሊያስቀጥል ይችላል?

አገራዊ አንድነት

ህወሓት በፈለገው ጊዜ ከኢትዮጵያ ገንጥሎ ታላቋን ትግራይን ለመምስረት እንዲችል በህገ መንግሥት ታሪክ ውስጥ ታይቶና ተሰምቶ የማያውቅ አንቀፅ ፫፱ን የመሰለ የመገንጠል መብት የሚሰጥ አንቀፅ በኢትዮጵያ ህገ መንግሥት ውስጥ ያካተተ ሲሆን፣ አሁን ያለው በኦሮሞ ብልፅግና የሚዘወረው መንግሥትም ታላቂቷን ኦሮሚያን የማዋለድ ኦነጋዊ ተልእኮ ስላለው ይህን የመሰለ ለአገር አንድነት ፀር የሆነ አንቀፅን የያዘ ህገ መንግሥት ይሻሻል ወይም ይለወጥ ሲባል በሬሳየ ላይ እያለ ነው። ሰሞኑን ከህወሓት ጋርም ስምምነት ላይ እንዲደርሱ ቁልፍ ሚና የተጫወተው ይኸው በህገ መንግሥቱ መከበር ላይ ያላቸው ፅኑ የሆነ ተመሳሳይ አቋማቸው ነው።

አንቀፅ 39 ለኢትዮጵያ መፍረስ የተቀበረ ጊዜ ጠብቆ የሚፈነዳ ቦምብ መሆኑን የማይገነዘብ የዋህ ብቻ ነው። ህገ መንግሥቱ በአዲስ ህገ መንግሥት ተተክቶ ነገድንና ቋንቋን መሰረት በማድረግ የተመሰረተዉ የክልል አወቃቀር ተወግዶ ሁሉንም ኢትዮጵያዊ በዜግነቱ ብቻ ዕኩል መብት በሚሰጥ የፌደራል አወቃቀር ይተካል ተብሎ ሲጠበቅ አንቀፅ 39ም እንደተከበረ ክልልም እንኳን ሊወገድ አዳዲስ ክልሎች እየተፈጠሩ ይገኛሉ። ሌሎችም ክልል የመሆን ጥያቄያቸውን አጠናክረው ቀጥለዋል። አንቀፅ 39ና የክልል አወቃቀር በመለስ ዜናዊ ይመራ በነበረው ህወሓት የተቀመረ ሲሆን የአሁኖችም ገዥወች ይህንን በመጠቀም ኢትዮጵያን የማፍረሱን ሂደት አጠናክረው ቀጥለውበታል።

ህዝብ

አንድ አገር ወይም ስርዓተ መንግሥቱ የሚመስረተው በህዝቡ መሆኑ አያጠያይቅም። ኢትዮጵያንና ስርዓተ መንግስቷን በማቆምና ነቅቶ ከመጣባት ሁሉ ጠላት በመጠበቅ ጉልህ ሚና ያለው የአማራ ህዝብ መሆኑ በግልፅ የሚታወቅ ሲሆን ነገር ግን ኢትዮጵያን በቅኝ ግዛት ለመያዝ በተለያየ ጊዜ ሞክረው ያልተሳካላቸው ኃይሎች የቅኝ ግዛት ህልማቸውን ያጨናገፈባቸው እንደ ህዝብ አማራው ነው የሚል ድምዳሜ ላይ በመድረሳቸው እንዲጠፋ ወይም እንዲዳከም በተለያየ ጊዜ ጥቃት እንዲደርስበት ሲያደርጉ ቆይተዋል። አሁን ደግሞ የእነርሱን ትርክት በተጋቱ ኃይሎችና የዘሩት የጥላቻ ዘር ፍሬውን አፍርቶ በሺወች የሚቆጠሩ አማሮች በኦሮሚያ ክልል በወለጋ በሰሜንና ምእራብ ሸዋ እንዲሁም በመተከል በአማራነታቸው መንግሥት መር የሆነ የዘር ማጥፋት ጭፍጨፋ ሰለባ እየሆኑ ይገኛል። የኢትዮጵያ መስራችና ጠባቂ የሆነውን የአማራን ማህበረሰብ መጨፍጨፍ ኢትዮጵያን ለማፍረስ ከሚደረጉት ሴራወች ውስጥ አንዱና ዋነኛው ጉዳይ ነው።

ሰንደቅ አላማ

በዓለም ላይ ያሉ አገሮች ሁሉ በውስጣቸው የሚኖሩ ዜጎችን ሁሉ አስተሳስሮ የሚይዝ የራሳቸው መለያ የሆነ ሰንደቅ አላማ አላቸው። ኢትዮጵያም መለያ የሆናት አረንጓዴ ቢጫ ቀይ ቀለማትን የያዘ ሰንደቅ ዓላማ አላት። ለዚህ ሰንደቅ አላማ መከበር ለአገር ነፃነትና ሉዓላዊነት በሽህ የሚቆጠሩ ኢትዮጵያን በጀግንነት በየጦር ግንባሩ ተፋልመዋል፣ ተሰውተዋል። አትሌቶችም በብዙ አለምአቀፍ ስፓርት የውዽር መድረኮች ድል በመንሳት ይህ ሰንደቅ አላማ በክብር እንዲውለበለብ እድርገዋል በማድረግም ላይ ይገኛሉ። ከአፍሪካ ምርጥ አየር መንገድ ተብሎ የተመሰከረለት የኢትዮጵያ አየር መንገድም ይህን አረንጓዴ ብጫ ቀይ ሰንደቅ አላማ በአውሮፕላኖቹ ላይ እንደመለያ በመጠቀም በዓለም ሰማይ እየበረረ ኢትዮጵያን እያስተዋወቀ ይገኛል።

የተለያዩ ብሔራዊ በዓላት እንዲሁም የኦርቶዶክስ ክርስትና ሃይማኖት ክብረ በዓላት ሲከበሩ አረንጓዴ ቢጫ ቀይ ቀለም ያለው ቲሸርት ነጠላ ቀሚስ ወዘተ ይለበሳሉ። ሆኖም አትልበሱ እየተባለ ሰዎች የሚደበድቡት የሚታሰሩት ብሎም የሚገደሉት ለምን ይሆን? ይህ ዜጎችን አስተሳስሮ ዘመናት የተሻገረ ሰንደቅ አላማ እየተገፋ የአንድ ክልል ወይም የአንድ ፓርቲ መለያ አርማ በምትኩ እንዲውለበለብ እየተሞከረ ያለው ሂደት ምንን ያመላክተናል?

ብሔራዊ መዝሙር

አገሮች ሁሉ ልክ አንድ ሰንደቅ ዓላማ እንዳላቸው ሁሉ የአገርን አንድነት የዜጎችን ፅኑ ህብረትና ለአገራቸው ያላቸውን የጋራ ፍቅርና በጠላት ቢጠቁ ለመስዋእትነት ዝግጁነታቸውን የሚገልፁበት ብሄራዊ መዝሙር አላቸው። ኢትዮጵያም የራስዋ የሆነ ብሔራዊ መዝሙር አላት። ይህ መዝሙር በየት/ቤቶች፣ በመከላከያ፣ፓሊስና ሌሎች ፀጥታ ክፍሎች፣ ማሰልጠኛወች፣ በስፓርት አደባባዮችና በሌሎችም ባልተጠቀሱ ቦታወች በጋራ እየተዘመረ ለአገር ክብርና ፅኑ አለኝታነት በማሳየት የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ይሰቀላል ወይም ይወርዳል። ታዲያ አሁን የኢትዮጵያ ህዝብ መዝሙር ተትቶ የክልል ህዝብ መዝሙር ያውም ህዝብን ከህዝብ የሚያጋጭ መልእክት የያዘ መዝሙር መዘመር አለበት ተብሎ በመንግሥት ትእዛዝ ለአቅመ አዳምናአቅመ ሄዋን ያልደረሱ ተማሪዎች መምህራንና ወላጆች ሲደበደቡ ሲታሰሩ ሲንገላቱ ማየት ምን ያሳየናል?

አርማ

አብዛኛው የአለም አገሮች የስርዓተ መንግሥታቸው ብሎም የአገራቸው መለያ አርማ ወይም ልዩ ምልክት አላቸው። ኢትዮጵያ ለረጅም ዘመናት ያስቆጠረ አንበሳን እንደ መለያ አርማዋ አድርጋ ስትጠቀም ቆይታለች። አንበሳውም የጥንካሬ የአሸናፊነት ምልክት በመሆን ጥሩ ስነልቦና በማጎናፀፍ በየአውደ ውጊያው አሸናፊ በመሆን አገርን ከጠላት በመጠበቅ ነፃነቷን የጠበቀች አገር ለማቆየት ተችሏል። ጣሊያን ዳግም በወረረችን ጊዜም እርበኞች የጥቁር አንበሳን ስያሜ የያዘ ጠንካራ ወታደራዊ ስብስብ በማቋቋም ጠላትን ተፋልመዋል። ይህ እንበሳ አርማችን በተለያዩ ቦታወች የነበረ ሲሆን በተለይም በቤተመንግሥት እጥር ግቢ በሮች ላይ በመሆን የአገራችንን ጥንካሬና አይበገሬነትን ለዓለም ሁሉ የሚያሳይ ነበር። ነገር ግን አሁን ባለው ጠቅላይ ሚኒስቴር ትእዛዝ ታሪካዊዉ አርማችን አንበሳ ተነስቶ በጣዖስ(ፒኮክ) እንዲተካ መደረጉ የምናውቃትን ኢትዮጵያን የማፍረስ አንዱ አካል መሆኑን መገንዘብ ይገባል።

ቋንቋ

አንድ መንግሥት ያለው አገር ሁሉም ዜጎች ሊግባቡበት የሚያስችል አንድ ቋንቋ ሊኖረው ይገባል። ኢትዮጵያም እንደሌሎች አገሮች ሁሉ ሁሉንም ኢትዮጵያውያንን እያግባባ ለዘመናት የዘለቀ የአማርኛ ቋንቋ አላት። ኢትዮጵያን ማፍረስ የሚፈልጉ ኃይሎች ግን አማርኛን ለማዳከምና ለማጥፋት ጥረት እያደረጉ ይገኛሉ። አዲስ በተቀረፀው ስርዓተ ትምህርትም አማርኛ በሁሉም ክልሎች ከአፍ መፍቻ ቋንቋቸው በተጨማሪ መማር እንዳለባቸው የሚያዝ ደንብ አልተቀመጠም። በአንድ አገራዊ በሆነ ቋንቋ መግባባት ያልቻለ ዜጋ እንዴት የዜጋዊ ግዴታውን በመወጣት አገርን አፅንቶ ሊያስቀጥል ይችላል? ከአማርኛ ሌሎች ተጨማሪ ቋንቋዎችይጨመሩ የሚለው አካሄድ በመርህ ደረጃ ጥሩ ሃሳብ ነው። ነገር ግን ሌሎች የሚጨመሩ ቋንቋዎች በጥናት ላይ የተመሰረተና መቼ እንዴት ይጨመሩ የሚሉት ሃሳቦች በደንብ መታየትይኖርባቸዋል። እንዲሁም ተጨማሪ ቋንቋዎች የሚሰጡት አማርኛን ለማዳካም በሚል እሳቤ መሆን ፈፅሞ የለበትም። በተጠና ፓሊሲ ተደጋጋፊ መሆን እንዳለባቸው ሆኖ መሰራት ይኖርበታል። አሁን እየተሄደበት ያለው ግን አማርኛን አዳክመን ኦሮሞኛን እናሳድጋለን የሚል በመሆኑ አገር አፍራሺ አካሄድ መሆኑ በደንብ መታወቅ ይኖርበታል። ፍትሀዊ ያልሆነ በጉልበት ስልጣንን መከታ አድርጎ የተጫነ ስለሆነ በደንብ ሊፈተሽ ይገባል።

ሃይማኖት

ሃይማኖት በአንድ አገረ መንግሥት ምስረታ ቀላል የማይባል አስተዋፅኦ አለው። በተለይም እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አገሮች አይነተኛ ሚና እንዳለው የማያጠያይቅ ሀቅ ነው። በተለይም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ኢትዮጵያን እንደ አገር በመመስረቱና አፅንቶ በማቆሙ አንፃር የነበራትና ያላት ሚና በጣም ከፍተኛ ነው። የእስልምና ሃይማኖትም በአገር ግንባታው የራሱን አስተዋፅኦ ማበርከቱ እሙን ነው። ነገር ግን አሁን ያለው መንግሥት የአገር ምሰሶ የሆኑትን በተለይም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያንን ለማዳከም ብሎም ለማጥፋት ሰፊ ስራወች እየሰራ ይገኛል። ለምሳሌ ከ ፶ በላይ አብያተ ክርስቲያናት ሲቃጠሉ ካህናትና በብዙ መቶወች የሚቆጠሩ ምእመናን ሲገደሉ ህግ ሲያስከብር ወንጀለኞችን ለፍርድ ሲያቀርብ አልታየም። እንዲያውም ለብልፅግና ካድሬወች ስልጠና ባዘጋጀው ሰነድ የኦሮቶዶክስና እስልምና ሃይማኖቶች ለብልፅግና ፀር እንደሆኑየሚያስተምር ፅሁፍ አሰራጭቷል። ለብልፅግና ፀር ተብሎ የተፈረጀ ደግሞ መዋከብና መዳከም አለበት ማለት ነው። የዚህን ውጤት ነው አሁን እያየን ያለነው። የመስቀል አደባባይ የጃን ሜዳ የጥምቀት ማክበሪያ ቦታወች ለመንጠቅ እየተሸረበ ያለው ሴራ የማታስተምራቸውን ታስተምራለች የሚል ሃይማኖታዊ ብጥብጥ ማስነሳት፣ ታቦት በዚህ አያልፍም ብሎ ወጣት ምዕመናንን መግደል፣ ማሰርና ማንገላታት፣ ይህ ሁሉ ጠላት ነው ብለው በፈረጁት ሃይማኖት ላይ በእቅድ የሚካሄዱ ተግባራት ናቸው።

ከኦሮሚያ ቤተክህነት እስከ የኦሮሚያና ብሄር ብሄረሰቦች ሲኖዶስ ማዋቀርና የጳጳሳት ህገ ወጥ ሲመት በፌደራል መንግሥትና በኦሮሚያ ብልፅግና ሙሉ ድጋፍ አዲስ የኦሮሚያ ቤተክህነትለማቋቋም በሚል ቤተክርስትያኒቷን ሲያምሷት መቆየታቸው ይታወሳል። በጀርባ ሆነው ይመሩ የነበሩት ሊቀጳጳስ ራሳቸዉን ፖትርያርክ ለማድረ ህገ ወጥ የጳጳሳት ሲመት መስጠታቸው ይፋ ሆኗል። ይህ ህገ ውጥ ድርጊት ያለ ተረኛው ኃይል ዕውቅናና ሙሉ ድጋፍ የማይታሰብ ነገር ነው። ተፈታ የተባለው የኦሮሚያ ቤተክህነት ምስረታ ጉዳይ በጣም በላቀ ደረጃ ገዝፎ መጥቷል። ቤተክርስቲያንም ሆነ ምዕመኑን ለመከፋፈል ብሎም አዲስ አገር ለማዋቀር ከሚደረገው ጥረት አንዱ አካል ይመስላል። ይህ ህገ ቤተክርስቲያንንና ቀኖናን ብሎም ሃይማኖትን የጣሰ ድርጊት በይቅርታና ስምምነት የተፈታ ቢመስልም ነገር ግን አሁን በቅርቡ ህገ ወጥ ቡድኑ በነቀምት ሌላ ከክልሉ ባለስልጣናት በሚደረግለት ድጋፍ ሌላ ደብር በጉልበት በነቀምት የደብሩን አስተዳዳሪ በማሰር ተቆጣጥረዋል። ይህ የፌደራልና የኦሮሚያ ክልል መንግሥት የጋራ ፕሮጀክት እንደቀጠለ ነው።

በትግራይም ጦርነቱን ሰበብ በማድረግ የተለየ የትግራይ ቤተክህነት አቁቁመናል ብለዋል። በእርግጥ ሌላ ሲኖዶስ ምስረታ ወይም ጳጳሳት ሲመት አላደረጉም። አሁንም ከቅዱስ ሲኖዶስ የተላከላቸውን መልዕክት አልተቀበሉትም። አገር የመሰረተችንና አገር አፅንታ ያቆየችና አሁንም አፅንታ የያዘች ቤተክርስቲያንን ለማጥፋት መስራት አገር የማፍረስተግባር አይደለምን? ምእመኑ በሙሉ ቁርጠኝነት በቅርቡ እንዳሳየው ከቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ ጋር መቆምና ቤተክርስቲያኑና አገሩን ከጥፉት ኃይሎች ሴራ የመጠበቅ ኃላፊነት አለበት። መንግሥት በቀኖና የሃይማኖትና ስርዓተ ቤተክርስቲያን ህግ በመጣስ በቅዱስ ሲኖዶሱ ከተወገዘዉ ህገ ወጥ ቡድን ጋር መወገኑ ግልፅ ነዉ። እንዲያዉም የብሄር ሲኖዶስ በማቋቋምለአዲስ አገር ምስረታ እየተዘጋጀ ይመስላል። ስለዚህ ይህን ዉለታ ቢስነትና እኩይ ተግባር ሁሉም ኢትዮጵያዊ ሃይማኖት ነገድ ሳይለይ ሊያወግዘዉና ሊታገለዉ ይገባል። የኢትዮጵያኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን በእርግጥም አገር ናት። እርሷ ተናግታ ኢትዮጵያ በምንም ተአምር ሰላም አትሆንም። ስለዚህ ሁሉም ዜጋ ለቤተክርስቲያኑና ለሀገሩ ሰላም ዘብ መቆምአለበት።

የግዕዝ ፊደላት

በአለም ውስጥ የራሳቸው ሆህያት ወይም ፊደላት ያላቸው በጣት የሚቆጠሩ አገሮች ናቸው። ከእነዚህም ውስጥ አንደኛዋ ኢትዮጵያ ነች። ታዲያ ሌሎች አገር የሚቀኑበትን የአገር ሃብት የሆነውን ግእዝ ቋንቋን መሰረት አድርገው የተገኙትን ፊደላትን ሁሉም የአገራችን ቋንቋወች መጠቀም ሲገባቸው ቅን ያልሆነ ፓለቲካን መሰረት ያደረጉ ኃይሎች በቀደዱት ቦይ በመፍሰስ ለምን ባእድ የሆነ የላቲን ፊደላትን መጠቀም አስፈለገ? ያውም ከኢኮኖሚ አንፃር ሲታይ በጣም አዋጪ አለመሆኑ እየታወቀ። ለምሳሌ በጥናት እንደተረጋገጠው የላቲን ፊደላትን ተጠቅሞ በቁቤ በአፋን ኦሮሞ ቋንቋ የተፃፈ 300 ገፅ ያለው መፅሐፍ በግዕዝ ፊደላት ቢፃፍ ከ100 ገፅ እንደማይዘል ነው። እንግዲህ አስቡት በቀላሉ ተጨማሪ 200 ገፅ ለመፃፍ የሚወስደው ጊዜና የሚባክነው ገንዘብ። ሌሎች የአፍሪካ አገሮች የአፍሪካ ቋንቋ አማርኛ ይሁን የሚሉትም ይህን የእኛን የግዕዝ ፊደላት እንደራሳቸው በመቁጠር ነው። ታዲያ እኛ ላይ ምን አዚም ተጭኖን ነው ይህን ማየት የተሳነን? ይህ ሂደት አገርን ፈፅሞ አያፀናም። አንድነትንም አያጠናክርም።

ታሪክ

ታሪክ በየዘመኑ የነበሩ ትውልዶችን አወንታዊም ሆነ አሉታዊ ክስተቶችን ሰንዶ የያዘ የአንድ አገር ወይም ህዝብ የጋራ ሀብት ነው። በአንድ ወቅት የተከሰቱ አሉታዊ ሁነቶችን እንደ መማሪያ በመውሰድ ዳግም እንዳይከሰቱ እንማርባቸዋለን። በአስተማሪነታቸው ጉልህ ሚና ያላቸውን ክስተቶች ደግሞ ትውልድን ለማስተማሪያነትና ለማበረታቻነት መጠቀም ይገባል። ኢትዮጵያ ከቀደምት ጥንታዊ ስልጣኔ ካላቸው አገሮች አንዱዋ እንደመሆኗ ብዙ አኩሪ ታሪክ ያላት ሃገር ናት። ነፃነታቸውን ሳያስደፍሩ የቆዩ አገራት በአለም በጣም ጥቂትሲሆኑ አንዷ ኢትዮጵያ መሆንዋ ይታወቃል። ይህ ህሉንም ኢትዮጵያዊ በጋራ የሚያኮራ ተግባር ነው። በአገረ ምስረታ ወቅት አንዳንድ አካባቢዎችየተለየበደልእንደተደረገባቸውና ከዚህም የተነሳ የኢትዮጵያታሪክ የእኛታሪክአይደለምየሚሉ ድምፆች ይስተጋባሉ። ለመሆኑ በየትኛው ዓለም ነው የአገረ መንግሥት ምስረታ እንዲሁ አልጋ በአልጋ የተካሄደው? ሀሉም አገራት ያለፉበት ታሪክ አላቸው። ታዲያ አንድም ህዝብ የአገሩን ታሪክ ታሪኬ አይደለም ብሎ የተነሳ አልታየም። ኢትዮጵያ ውስጥ ግን ያለንን እለም የሚቀናበትን ታሪክ በርዘን ሌላ ያልነበረ አዲስ ታሪክ እንፍጠርተብሎ በሰፊው እየተሰራበት ያለው ሁኔታ አገር ያፈርሳል እንጅ ስለማያፀና በአስቸኳይ መታረም አለበት። ደግም ሆነ ክፉ ታሪካችን የጋራ ታሪክ ነው፣ እንወቀው እንመርምረው እንማርበት እንተባበርበት። ታሪካችን በብዙ ትውልድ የተሰራ አያት ቅድመ አያቶቻችን አባት እናቶቻችን በጋራ ሰርተው የተውልን ስለሆነ እናክብረው፣ መዘከር ያለበትን እንዘክረው።

ዋና ከተማ፡ የአዲስ አበባ ከተማ ጉዳይ

በአለም ያሉ አገራት በሙሉ የአገረ መንግሥታቸው ዋነኛ ማእከል ሆኖ የሚያገለግል ዋና ከተማ አላቸው። ኢትዮጵያም አዲስ አበባን የመሰለ ውብ ዋና ከተማ አላት። አዲስ አበባን ካለችበት ደረጃ ለማድረስ ሁሉም ኢትዮጵያዊ በተለያየየ ትውልድ ዘመን የበኩሉን አስተዋፅኦ አድርጓል። በመሆኑም አዲስ አበባ የሁሉም ኢትዮጵያዊ በእኩልነት የጋራ ሀብት ናት። ይህ ምንም ጥያቄ ውስጥ ሊገባ የማይችል ሀቅ ሆኖ እያለ ነገር ግን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አዲስ አበባ የእኔ ናት ሌላው እስከፈቀድንለት ድረስ መኖር ይችላል የሚል ኃይል ተነስቷል። ይህ ፈፅሞ አገር አፍራሺ አካሄድ በመሆኑ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ሊታገለውና ሊያስቆመው ይገባል። ሌላው መለስ ዜናዊ ከፋፍሎ ለመግዛት እንዲያመቸውና ኦሮሞውን በአዲስ አበባ ኗሪነት ቁጥሩ በጣም ከፍተኛ ከሆነው የአማራ፣ የጉራጌና ሌላው ሕዝብ ጋር ለማጋጨት በህገ መንግሥቱ ውስጥ ኦሮሚያ ከአዲስ አበባ ልዩ ጥቅም ታገኛለች የሚል አንቀፅ አስፍሯል። ይህም አያስኬድም። በአንድ አገር ውስጥ እየተኖረ ልዩ ተጠቃሚ የሚል ነገር አይሰራም። ህጋዊ ወይም ሌላ አመክንዮም የለውም፥ ብሎም አንድነትን ይሸረሽራል። ይህ አንቀፅም መወገድ አለበት፣ እስኪወገድ ድረስ ተግባራዊ እንዳይሆን አጥብቆ መታገል የግድነው። ይህ አሁን ካልተገታ በሌላ ጊዜ ጉልበት የተሰማው ሁሉ እየተነሳ ከአዲስ አበባም ሆነ ሌሎች ለምተው ከሚገኙ ከተሞች ወይም አገራዊ መሰረተ ልማቶች ልዩ ጥቅም ይገባኛል የሚል የማያባራ ትርምስ ውስጥ ሊከት ይችላል።

ወደ አዲስ አበባ መግባት አትችሉም ከጎንደርና ከጎጃም እንዲሁም ከወሎና ሰሜን ሸዋ ወደ አዲስ አበባ ለተለያየየ ጉዳይ የህዝብ ትራንስፓርት ይዞ ከሚመጣው ህዝብ ውስጥ አማራው እየተለየ እንዳይገባ እየተከለከለ ስንቱ ተንገላታ። ይባስ ብሎ ክጎጃም መስመር ወደ አዲስ አበባ የሚጓዙ አማራወች እየተለዩ በኦነግ ታጣቂወች ይዘረፋሉ፣ ይገደላሉ። ብዙዎች እየተታገቱም በብዙ መቶ ሺህ ብር ወይም ሚሊዮን እያስከፈሉ ይለቃሉ፤ መክፈል ያልቻለውን ይገድላሉ። ይህ ሁሉ ወንጀል የሚፈፀመው በኦሮሚያ ክልል ዉስጥ ነው። ይሀ እስከ መቼ ነው የሚቀጥለው?

የድሬዳዋ ከተማ ጉዳይ

የድሬዳዋ ከተማ ህወሓት በትረ ስልጣኑን ከመረከቡ በፊትም ራስ ገዝ ከተማ እንደነበረች ይታወቃል። ከዚያም በቻርተር ራሷን ችላ የምተዳደር ከተማ ሆና እንድትቀጥል ተደርጎ ይኸው እስከዛሬ ደርሳለች። ነገር ግን ምንም የህግ አግባብ በሌለው ሁኔታ በፓለቲካ ውሳኔ 40 40 20 በሚል ማለትም 40% ውክልና ለኦሮሞ 40% ውክልና ለሶማሌ 20% ለተቀረው ኢትዮጵያውያን ተብሎ እየተሰራበት መቀጠሉ እጅግ አሳዛኝ ነው። ሁሉም የከተማዋ ነዋሪዎች እኩል መብት ሊኖራቸው ሲገባ ስልጣን ለመያዝ፣ ስራ ለመቀጠር፣ ንግድ ለመክፈት፣ ቤት ለመስራት ይህንን ዘግናኝ የሆነ ቀመር መሰረት አድርጎ ነው። ይህ የአፓርታይድ አገዛዝ ዋናው መገለጫ ሲሆን ህወሓት ከስልጣን ከተገፋ በኋላም እየተሰራበት መቀጠሉ በጣም የሚገርምና የአሁኑ ተረኞች ከበፊቶቹ ጋር በባህሪ አንድ መሆናቸውን በግልፅ ያሳያል።

 ሁሉምየከተማዋነዋሪዎችበእኩልነትየፓለቲካውክልናኖሯቸውራሳቸውንበራሳቸውማስተዳደርሲገባ ኦሮሞና ሶማሌ እየተፈራረቁ ያስተዳድሯት ማለት ምን ማለት ነው? ሌላው ነዋሪስ ለምን መብቱ አልተከበረለትም? ይህ የተበላሸ አሰራር መስተካከል ሲኖርበት ይባስ ብሎ ከነጭራሹ ድሬዳዋን ወደ ኦሮሚያ ጠቅልሎ ለመውሰድ ሺር ጉድ መጀመሩ ወዴት እያመራን ይመስላችኋል? ይህ ጉዳይ በቶሎ ካልተገታ ለከፍተኛ የእርስ በእርስ ግጭት ብሎም አገር የማፍረስ ኃይል ያለው እልቂት ስለሚያስከትል ሁሉም ኢትዮጵያዊ ድምፁን ማሰማት ይጠበቅበታል።

የአዲስ አበባ የኦሮሚያ ክልል ዋና ከተማነት

አሁን ባለው ህገ መንግሥት መሰረት አዲስ አበባ የኢትዮጵያ ዋና ከተማ ናት እንጅ የኦሮሚያ ክልልም ዋና ከተማ ናት አይልም። መለስ ዜናዊ ለፓለቲካ ትኩሳት ማስታገሻነት ለመጠቀም ሲፈልግ የኦሮሚያ ክልል ከተማ አዲስ አበባ ሳይፈልግ አዳማ እያለ የቆየ ሲሆን የኦሮሚያ ክልል መንግሥት አዲስ አበባ የክልሉ ዋና ከተማ ናት ቢልም የክልል ህገ መንግሥት የአገሪቱን ህገ መንግሥት መፃረር ስለማይችል ይህ አዲስ አበባ የኦሮሚያ ክልል ዋና ከተማነት ህጋዊነት የለውም። ሌላ የፌደራል አወቃቀር ሲተገበር መልስ እንደሚያገኝ ጥርጥር የለውም። የአዲስ አበባና የኦሮሚያ ወሰን የማካለል ስምምነት ተደረሰ መባልና ሸገር የሚባል ከተማ ምስረታ በኦሮሚያ ክልልና በአዲስ አበባ ከተማ መስተዳደር መካከል ሁለት አመት የፈጀ ውይይት ተካሂዶ የወሰን ስምምነት ላይ ተደርሷል የተባለው ፈፅሞ ህጋዊነት የለውም። ምክንያቱም ይህን መሰል ጉዳይ በአንድ የነገድ ፓርቲ ውስጥ በሚሚወክሉ ጠቅላይ ሚንስትር የክልልፕሬዜዳንትና የከትማዋ ከንቲባ መካከል የተካሄደ ድብቅ ድርድርና ስምምነት በመሆኑ ነው። በተጨማሪም ነዋሪው ህዝብ በቀጥታም ሆነ በወኪሎቹ በኩል ስለ ጉዳዩ መወያየት ይገባዋል። በተጨማሪማ በፌደራል ስር የምትተዳደር የቻርተር ከትማ ስለሆነች ሌሎች ክልሎችም በጉዳዩ ገብተው መወያየት አለባቸው። ይህ ስምምነት መሰረዝ ይኖርበታል።

ይህን የደረሱበትን ህገወጥ ስምምነት ተከትሎ አምስት አዲስ አበባ ዙሪያ ያሉ ከተሞችን በአንድ ላይ አድርገው በኦሮሚያ ክልል ውስጥ ሆኖ ሸገር የሚል ከተማ ፈጥረዋል። በፍጥነትም ብሄርን መሰረትያደረገ በሰፊው ቤቶችን ማፍረስ ጀምረዋል። ይህ አማራውን ከወለጋ ማፅዳት የሚለው ፕሮጀክት ተቀጥላ የሆነ በዚህ በሸገር ባሉት ከተማ ለገጣፎ ለገዳዴ ሰበታ ገላን ሱልልታ በተባሉት ከተሞች እየፈፀሙት ይገኛሉ። በአስር ሺህ የሚቆጠሩ አማሮች ጋሞወች ጉራጌወችና ወላይታወች ቤት አልባ ሆነው ሜዳ ላይ ተጥለዋል። በሚያሳዝን መልኩ በጅብ የተበሉ ህፃናትም እንዳሉና እንዲሁም ግፉን መሸከም አልችል ብለው ራሳቸውን ያጠፉ ሰወችም እንዳሉ ተሰምቷል። ይህ ፍፁም ህገ ወጥና የተረኝነት ጥግ አካሄድ አገር የሚያፀና ይመስላችኋል? ይህ ህገ ወጥ የከተማ ፈጠራና የዜጎችን ቤት ማፍረስ እብደት በአስቸኳይ መቆም አለበት። ሁሉም ኢትዮጵያዊ ሊያወግዘውና ሊታገለው ይገባል።

የድል በዓላት

ኢትዮጵያ ነፃነቷን ጠብቃ ለመቆየት ያስቻሏት አያሌ ጦርነቶች ተሳትፋ በድል አድራጊነት ስታጠናቅቅ ቆይታለች። ይህን ደግሞ ታሪክ የመዘገበው ሀቅ ነው። ከድሎቹ ሁሉ አንፀባራቂ የሆነውና የአውሮፓውያንን የዘላለም አፍሪካን ተቀራምቶ የመግዛት ህልም ጥያቄ ውስጥ የከተተውና ነጭ በጥቁር ህዝብ በመሸነፍ የመጀመሪያውና የአለምን ታሪክ አውድ ቀያሪ ተብሎ የተወሰደው ኢትዮጵያ በጣሊያን ላይ የተቀዳጀችው የአድዋ ድል ነው። ይህ ለአፍሪካ ብቻ ሳይሆን ለጥቁር ህዝብ ሁሉ የነፃነት ጮራ ፈንጣቂ ድል በመላው አፍሪካ እንዲከበር እንቅስቃሴ በተጀመረበት በአሁኑ ወቅት ግን በአገራችን በኮሰሰ መልኩ እንዲታሰብ ይባስም ብሎ የድሉ ዋና መሪወችን አፄ ሚኒሊክንና እቴጌ ጣይቱ ሳይዘከሩ እንዲሁም ይከበርበት የነበረው የእድዋ ድል አደባባይ ቀርቶ ሌላ ቦታ እንዲከበር መደረጉ ምን የሚሉት አካሄድ ነው? ይህ የድሉን መሃንዲሶች አፄ ሚኒሊክን እና እቴጌ ጣይቱን ሳያወሱ የአድዋ በዓል ይከበር የሚለው ነውረኛ አካሄድ በዚህ አመትም እንዲደገም በመንግሥት ደረጃ እየተሰራበት መሆኑ እጅግ ያስቆጫል። ይህ አካሄድ እውነት አገር ያፀናል? ድሉ የጋራችን ነው ድሉም ያለ መሪ አልመጣምና ድሉን ፈልገን መሪወችን ማንኳሰስ አስተዋፅኦቸውን ለመዘከር አለመፈለግ ፈፅሞ አይሰራም። ህዝቡ አጥብቆ ሊታገለው ይገባል። እንደነዚህ አይነት ውለታ ቢሶችንና ታሪክ ከሃዲወችን በቃችሁ ሊላቸዉ ይገባል።

ቅርስ

የአገራት ታሪክ ከትውልድ ትውልድ የሚተላለፈው ከፅሁፍ ማስረጃወች በተጨማሪ በቅርሶች አማካይነት ነው። ኢትዮጵያም ታሪኳን በቅርሶች አማካይነት ለትውልድ ለማስተላለፍ የቅርስ አጠባበቅ ህጎችና ደንቦችን አውጥታ አየሰራችበት ቆይታለች። ነገር ግን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ዘመቻ በሚመስል መልኩ የአገሪቱ ቅርስ ተብለው የተያዙ ቦታወችን አደባባዮችን ቤቶችን ልማት በሚል ሰበብ በማፍረስ ላይ ይገኛሉ። ይህ የታሪክን ሪከርድና አሻራ የማጥፋት ወይም ታሪክን የማዛባት አንዱ አካል ስለሆነ ሊቆም ይገባል። በተለይም በአዲስ አበባ በስፋት እየተተገበረ ይገኛል። ለምን ?

ባህል

በአንድ አገር ውስጥ የሚኖሩ የተለያዩ ማህበረሰቦች የተለያየ ባህል እንደሚኖራቸው ይታወቃል። ጎጂ እስካልሆነ ድረስ አንዱ የሌላውን ባህል አክብሮ በመደጋገፍ ይኖራሉ። በአዲስ አበባ ከቅርብ አመታት ወዲህ መከበር የተጀመረው የኢሬቻ በዓል ባህልን ሽፋን አድርጎ የሚካሄድ የባእድ አምልኮ ስርአት ነዉ እየተባለ ስለ ሁኔታው በደንብ የሚያውቁ የሃይማኖት ሰዎች ሳይቀር እየተናገሩ ይገኛሉ። ይህ ጊዚያዊ ስልጣንን መከታ በማድረግ ህዝብን ግራ እያጋባ ያለ በአል በግድ አዲስ አበባ አምጥቶ ማክበር ምን አመጣው? ባህልን ለፓለቲካ አላማ ማስፈፀሚያነት መጠቀሙ ህዝብን ያራርቃል እንጂ አያቀራርብም። እንደዚሁም ኢትዮጵያውያን የራሳቸውን ባህል ለማሳደግ ከመትጋት ይልቅ ብዙ የተለያዩ የዉጭ አገራት ባህሎች አንዳንዴም ከእኛ ባህል ጋር የማይሄዱ ባህሎች በሰፊው እየገቡ ይገኛሉ። ይህንን የሚከላከል የሚያስተምር ስራ ሲሰራ አይታይም። ነገር ግን በጣም አስፈላጊ ጉዳይ መሆኑ ሊታወቅና ተገቢ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል።

ነገስታትና አርበኞች

የአብዛኛው የአለም ሀገራት ታሪክ እንደሚያሳያው በሀገር ምስረታ ጉልህ ሚና የነበራቸውን ነገሥታት አርበኞች ማወደስ መዘከር ብሎም ሀውልት አቁሞ ከትውልድ ትውልድ ማስተላለፍ የተለመደ ተግባር ነው። በኢትዮጵያም ይህ ነው ሲደረግ የኖረው። ኢትዮጵያን አምርረው የሚጠሉት ህወሓትና ኦነግ ወደ በትረ ስልጣኑ ከመጡ ሰላሳ ሁለት አመታት ወዲህ ግን ለአገር ግንባታና አንድነት የደከሙ ነገሥታትን ማናናቅ ስማቸዉን ማጠልሸት ያልሰሩቱን ጥፋት መደረት የተለመደ ጉዳይ ሆኗል። ለምሳሌ አፄ ቴወድሮስንና አፄ ሚኒሊክን መጥቀስ ይቻላል። ሃውልታቸውን ለማፍረስም ብዙ ጊዜ ሞክረው በህዝብ ትብብር ከሽፏል። ነገር ግን የራስ መኮነንን ሀውልት በሀረር ከተማ ማፍረስ ችለዋል። የእቴጌ ጣይቱ ሀዉልት በአዲስ አበባም ሆነ በትዉልድ ቦታቸዉ ደብረ ታቦር እንዳይሰራ ከልክለዋል። የአርበኞችንም ታሪክ ማዛባት ወይም የእኔ ነው የሚል አስነዋሪ ተግባር ቀጥለዋል። ደጃዝማች በላይ ዘለቀን ኦሮሞ ነው የሚለውን ማስታወሱ ይበቃል። ይህ በነግሥታትና በአርበኞች ላይ የተነጣጠረው የተቀነባበረ ዘመቻ በኢትዮጵያ ታሪክ ላይ የተነጣጠረ መሆኑን ተረድተን ልንታገለው ይገባል።

ተረኝነት

ባለፈው የህወሓት ዘመን ባንኩንም ታንኩንም ከአንድ ነገድ በወጡ ሰዎች በመያዝ እንዲሁም የአገሪቱን ኢኮኖሚ ኤፈርት የሚል ኩባንያው ስር ጠቅልሎ በመያዝ ኢትዮጵያን እንደ ግል ንብረቱ ሲፈነጭባት ፍትህ ጠፍቶ ሺዎች በእስር ሲንገላቱ ሲገደሉ ይህ ሁሉ ስቃይ ያንገፈገፈው ህዝብ ለመብቱ በመነሳት ታግሎ ከአራት ኪሎ ስልጣናቸው እንዲለቁ ማድረጉ ይታወሳል። ህዝቡ በትግሉ ካመጣው ለውጥ የጠበቀው የህወሓትን ርእዮተ-አለምም ሆነ ይመራባቸው የነበሩ ዋና ዋና ፓሊሲዎች ተለውጠው በፍትሀዊ አስተዳደር እንዲተካ ነበር። ነገር ግን የሆነው ህዝቡ ከጠበቀው በተቃራኒው ሲሆን ህወሓትን በኦህዴድ ምስለኔዎች በመቀየር ምንም ሳያስቀሩ ህወሓት ያደረገውን በሙሉ እንዲያውም በባሰ መልኩ መተግበር ነው። ይህ ነው ተረኝነት የተባለው። ይህ የተረኝነት ዳፋ አቅመ አዳም ባልደረሱ ተማሪዎች ላይም እየደረሰ ይገኛል። በአዲስ አበባ የመለስተኛና የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች በኦሮሚያ ባንዲራ ስቀሉ በሚል እየደረሰባቸው ያለውን እስርና እንግልት ማስታወሱ በቂ ነው። ተረኝነቱ እየተገለጸበት ያሉበት ሁኔታወች ብዙ ናቸው።

ሌሎች ክልሎች ራሳቸውን በራሳቸው እንዳያስተዳድሩ ከማድረግ እንዲሁም ሁሉም የኦሮሞ ነው ወደሚል የለየለት እብደት ተሸጋግሮ አዲስ አበባን ለመጠቅለል እንዲሁም ኦሮሚያን ከሚያዋስኑ የሶማሌ ሲዳማ ጋምቤላ ቤንሻንጉል እና አማራ ክልሎች ጋር የመሬት ይገባኛል ግጭት ውስጥ ገብተዋል። የትምህርት ስርዓቱንም በመቆጣጠር ስርዓተ ትምህርቱን በፈለጉት መንገድ በመቅረፅ ላይ ተጠምደዋል። ይህ የተረኝነት አካሄድ በጊዜ ካልተገታ አገር የማፍረስ ከፍተኛ አቅም አለው። ከአባቶቻችን የተረከብናትን የምናዉቃትን ኢትዮጵያን እያፈረሳትም ይገኛል።

ፋኖን ማጠልሸት

ፋኖነት አማራነት ነው አማራነት ፋኖነት ነው ተብሎ በተደጋጋሚ የተገለፅ ጉዳይ ነው። ፋኖ አገር ሲወረር፣ ፍርድ ሲጓደል ክህዝብ ወግኖ በመቆም አገርን ወይም አካባቢውን ከወራሪው ኃይል ይታደጋል። በታሪኩ ይህን ሲያደርግ ኖሯል፤ አሁንም በቅርቡ ህወሓት ያደረሰውን አገር የማፍረስ ወረራ መከላከያና ከልዩ ኃይሉ ጋር በመተባበር ጠላትን አሳፍሮ በመመለስ አገርን ከመፍረስ መንግሥትን ከመገርሰስ አድኗል። የፋኖ ተግባሩ ይኸ ሆኖ እያለ ለምን የፋኖ መኖር እንቅልፍ ይነሳቸዋል? ፋኖን ኢመደበኛ፣ ፅንፋኛ፣ ፋኖ የአማራ ሸኔ እያሉ ያልሆነ ስም በመስጠት ለማዳከም ብሎም ለማጥፋት ሌት ከቀን የሚደክሙት በጣም አስገራሚ ነው። የፋኖ ውለታ ይህ ሆነና ከ18 ሺህ በላይ ፋኖወች በእስር ይገኛሉ።ወንጀላቸው ቅራቅር ላይ የህወሓትን ወራሪ ሰራዊት ድባቅ መተው መመለሳቸው የታፈነውን የመከላከያ ሰራዊት ከአፈና ማውጣታቸው ቀጥሎም ወደ አዲስ አበባ እየገሰገሰ የመጣውን ህወሓት ከደብረ ሲና መመለሳቸው ይሆን? ፋኖን በዚህ መልኩ እያሳደዱ ከአማራው ጋር በሰላም መኖርይ ቻላል ብሎ እንዴት ይታሰባል? ፋኖን ለቀቅ ማድረጉ ነገ ዛሬ የማይባል ጉዳይ ሲሆን የታሰሩትን ፋኖዎች በሙሉ ከነ ከነ መሪወቻቸዉ በሙሉ ለምሳሌ አርበኛ ዘመነ ካሴ በአስቸኳይ ከእስር መልቀቅ ይገባል።

የወልቃይትና ራያ ጉዳይ

ህወሓት ወልቃይትን ከጎንደር ራያን ደግሞ ከወሎ 1984 ዓ.ም ህገ መንግሥቱ ከመፅደቁ አራት አመት በፊት በጉልበት ስልጣኑን ተጠቅሞ ወደ ትግራይ እንዳካለላቸው በግልፅ እየታወቀ ከ፴ አመታት በላይ የደረሰባቸው ሰቆቃና የዘር ማጥፋት ጭፍጨፋ ሳያንስ ሁለት አመት ሙሉ ያለምንም በጀት እንዲሰቃዩ ማድረግ አግባብነት ያለው ስራ ነውን? ይልቁንም ህዝቡ በከፈለው መስዋእትነት መልሶ በእጁ ያስገባቸውን በሰላም ስምምነት ሰበብ በህገ መንግሥት መሰረት ያልተወሰዱትን አሁን ህገ መንግስቱን መሰረት አድርጎ ይወሰናል መባሉ በእውነት አማራው ወልቃይትና ራያን ለዳግም ባርነት እንዲሁ አሳልፎ ይሰጣል ተብሎ ታስቦ ነው? ወይንስ አንድ ጦርነት አቁሞ ወደ ሌላ ጦርነት ለመሸጋገር ነው የታሰበው? ደግሞስ የህወሓት ዋና እቅድ ወልቃይትና ራያን ይዞ ነፃይቷን ትግራይን መመስረት መሆኑ እየታወቀ፣ ብሎም ያለ ወልቃይትና ራያ ይህን የነፃነት ጥያቄ እንደማያነሳው እየታወቀ ሌላ አገር በማዋለዱ ሂደት እየተባበርነው ይሆን? የወልቃይትና የራያ ጉዳያ በጥንቃቄ ካልተመለሰ አገር የማፍረስ አቅም እንዳለው በደንብ መገንዘብ ይገባል።

የመተከልና ደራ ጉዳይ

እንደሚታወቀው ከ1984 ዓም በፊት መተከል የጎጃም ክፍለ ሀገር ከሰባቱ አንዱ አውራጃ ነበር። ህወሓት ታላቋን ትግራይን ስትመሰርት ለመጠቅለል እንዲመቻት መተከልን ከጎጃም አሶሳን ከወለጋ በመንጠቅ ፈፅሞ በታሪክ ያልነበረ ቤንሻንጉል ጉምዝ የሚልክልል አዋቀረች። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በመተከል አማራው በማንንቱ እየተጨፈጨፈ ይገኛል። ተረኞቹ ደግሞ የህዳሴ ግድብ ያለበት ቁልፍ ቦታ ስለሆነ ወደ ኦሮሚያ ለመጠቅለል ሰፊስራወች እየሰሩ ነው። አማራውንም ክምንጊዜውም በከፋ መልኩ እየጨፈጨፉት ይገኛሉ። ህዝቡ ግን ማንንቴ ይከበርልኝ እኛ አማራ ነን፣ አገው ነን፣ መተዳደር የምንፈልገው በአማራ ክልል ውስጥ ነው፣ እያለ ጥያቄውን ካነሳ አመታት ተቆጥረዋል። ሌላዉ እንደሚታወቀው 90% የሚሆነው የደራ ነዋሪ አማራ ሆኖ እያለ በኦሮሚያ ክልል ውስጥ በመካተቱና ብዙ አስተዳደራዊ በደል ማንነት ጭፍለቃ፣ ርስት ነጠቃ እየተካሄደበት በመሆኑ ወደ አማራ ክልል ለመመለስ ወይም ልዩ ዞን እንዲሆን ጥያቄ ካቀረበ የቆየ ቢሆንም ያገኘው ምላሽ ግን በኦሮሚያ ክልል በሚታገዙ ታጣቂወች ተደጋጋሚ ወረራ ነው። የመተከልና የደራ ጥያቄወች መልስ ሳያገኙ አገርን አፅንቶ በሰላም መቀጠል የማይታሰብ ነገር ነው።

ማህበራዊ መስተጋብር

ኢትዮጵያውያን ከሚታወቁበት ዋናው እሴታቸው ጥብቅና ጥልቅ የሆነ፣ ሃይማኖትና ነገድ የማይገድበው ማህበራዊ ትስስራቸዉ ነው። ይህ ማህበራዊ ትስስራቸው በደስታም ሆነ በሀዘን ወይም ችግር ባጋጠመ ጊዜ ሁሉ ተረዳድተው እያለፉበት ለሺህ ዘመናት ዘልቀዋል። የሃይማኖት በአላት ሲያከብሩ ሙስሊሙ ለክርስቲያኖቹ ክርስቲያኖች ለሙስሊሙ ማህበረሰብ የሚያሳዩት ትብብር እጅግ አስደናቂና በየትም አለም የማይገኝነው። ኑሯቸውን ለማሻሻልም እየተጠቀሙበት ይገኛሉ። እቁብና እድርን እዚህ ላይ መጥቀስ ይቻላል። ሌላው የጉርብትና ግንኙነታቸው በጣም አስገራሚ ከመሆኑ የተነሳ ከሩቅ ዘመድ የቅርብ ጎረቤት በሚል ብሂል ተባብረውና ተረዳድተው ይኖራሉ። ነገር ግን ህወሓት ክልልን ነገድንና ቋንቋ መሰረት አድርጋ ህዝብን ከከፋፈለች ወዲህ ብሎም አሁን ያለው ተረኛው ቡድን በተጠናከረና በባሰ ሁኔታ እየቀጠለበት ስለሆነ ህዝቡ ነቅቶ ተረኛውን ቡድን በቃህ ካላለውና ተፈላጊው ለውጥ ካልመጣ ይህ ኢትዮጵያውያን ያላቸው ማህበራዊ መስተጋብር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሸረሸረ ስለሆን ብሎም ከነጭራሹ እንዳይበጣጠስ ያሰጋል።

ማህበራዊ እሴቶች

ኢትዮጵያውያን ለዘመናት የቆዩና በመፍትሄነታቸው የተመሰከረላቸው ብዙ ማህበራዊ እሴቶች አሏቸው።ከነዚህም ውስጥ ዋነኞች ታላቅን ሽማግሌን ባልቴትን የሃይማኖች አባቶችን ማክበርና እንዲሁ የሽምግልና ስርአትን በመጠቀም ማንኛውንም በማህበረስብ ወይም በቤተሰብ ወይም በሁለት ግለሰቦች መካከል የተፈጠረን ግጭት ወይም አለመግባባት በእርቅ የመፍታትባህል ነበር። ይህ በመንግሥት ታላላቅ ሹሞች እስከ ንጉሶች መካከል የተነሳን ፀብ ወይም ጦርነት ሰላማዊ መፍትሄን እስከማስገኘት የዘለቀ ነበር። ነገር ግን እነዚህ ህዝብን አስማምተው ለዘመናት የቆዩ ኢትዮጵያዊ እሴቶች በስልት ተሸርሺረው ምንም ፋይዳ እንዳይሰጡ ተደርገዋል። ለምን?

የአኖሌ ሃውልት

አፄ ሚኒሊክ የኢትዮጵያን አንድነት ለማስከበር ባደረጓቸው ዘመቻወች ወቅት አሩሲ ውስጥ በተደረገ ውጊያ ወቅት ወታደሮቻቸው ህዝብ ፈጅተዋል ጡት ቆርጠዋል በሚል ያልተረጋገጠ ትርክት የአኖሌን ሃውልት ማቆም በእውነቱ ህዝብ ከህዝብ ተቀራርቦና ተባብሮ ለመኖር ያስችላል? ይህ የሃሰት ትርክት የተፈፀመ ለመሆኑ በደንብ ተመርምሮ ተፈፅሞ ከሆነ በታሪክ መፃህፍት ተካቶ እንድናውቀውና ዳግም እንዳንፈፅመው ማድረግ ሲገባ ለምን ይህን የጥላቻ ሀውልት መትከል አስፈለገ? ለመሆኑ ሁሉም ጉዳቱን በሀውልት ልግለፅ ቢል ስንት የጥላቻ ሀውልቶችን መትከል ይኖርብን ይሆን?

የክልል አወቃቀርና በሰላም የመኖርና ከቦታ ወደ ቦታ በነፃነት ተዘዋዉሮ የመስራት መብት አለመከበር የአንድ መንግሥት ተቀዳሚ ተግባሩ የዜጎችን በህይወትና በሰላም የመኖር ከቦታ ወደ ቦታ በነፃነት ተዘዋዉሮ የመስራትን መብት ማስከበር ነው። ነገር ግን አንድ አገር በሆነች ኢትዮጵያ የሚኖር ህዝብ ነገድንና ቋንቋን መሰረት ያደረገ የክልል አወቃቀር አንዱን ባለቤት ሌላውን መጤ ብሎ በመከፋፈል ዜጎች ዋና የመኖርና ተዘዋዉሮ የመስራት መብታቸውን በመጨፍለቅ ሺወች እየተጨፈጨፉ ሚሊዮኖች እየተፈናቀሉ ይገኛሉ። ይህ የክልል አወቃቀር በአስቸኳይ እልባት ካላገኘ የአገርን መፍረስ ከእውን ለማድረስ እየተቃረበ ነው ለማለትያ ስደፍራል። የክልል አወቃቀሩ በኢትዮጵያ እየደረሰ ላለው እልቂት ከዋነኛ ምክንያቶች ውስጥ አንዱ መሆኑ እየታወቀና በሌላ የአስተዳደር አወቃቀር መተካት አለበት እየተባለ በስፋት እየተጠየቀ ባለበት በአሁኑ ወቅት ሌሎች አዳዲስ ክልሎችን ማዋቀር ለምን ተፈለገ? ደግሞስ ለአንዱ ፈቅዶ ሌላውን መከልከል ምን የሚሉት አካሄድ ነው? የደቡብ ክልልን አሁን እያመሰ ያለው ሁኔታ ይህ ክልል ልሁን አትሆንም የሚል የፓለቲካ አቲካራ ነው። ሁለት አዲስ ክልሎች እንዲዋቀሩ ፈቅዶ እንዲሁም እንድ ሌላ ክልል እንዲፈጠር በዝግጅት ላያ ያለ መንግሥት ለምን የጉራጌና የወላይታን ህዝብ ክልል እንሁን ጥያቄያፍናል? ከላይእንደገለፅሁትክልልመፍረስእንዳለበትየታመነሆኖግንየማይፈርስከሆነለአንዱፈቅዶ ለሌላው መከልከል አግባብ አለመሆኑን ለማሳየት ነው። ኢትዮጵያ በአራቱም አቅጣጫ ሰላም ርቋት ቁም ስቅሏን እያየች ትገኛለች።

የተዛባ የህዝብ ቁጥር ቀመር ያመጣው ጣጣ

ኢትዮጵያ አሁን ለገባችበት ውስብስብ ችግር ከከተቷት ችግርች አንዱ የተዛባ የህዝብን ቆጠራ ስሌትና ይህንን ስሌት መሰረት አድርጎ ይገባኛል የሚባሉ የፓለቲካ ስልጣን የተለያዩ የመንግሥት አመራር ቦታወች በፀጥታ መዋቅሩ ውስጥ የሚገኝየአመራርቦታየኢኮኖሚናፋይናንስተቋማትአመራርየህዝብግንኙነትናየሚዲያተቋማት አስተዳደር ቦታዎች የበጀት ቀመር አወጣጥና የመሰረተ ልማትና የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት የመሳሰሉትን መፈጠራቸው ነው።

በአሁኑ ሰአት ገዥው የኦሮሞ ብልፅግና በድፍረት አፉን ሞልቶ ተረኝነት የሚባል የለም የያዝሁትን ቦታ ሁሉ የያዝሁት የምወክለውን የኦሮሞን ህዝብ ቁጥር መነሻ አድርጌ ነው የሚለው። የህዝብ ቆጠራው ግን እንደ ስሌታቸው እንዳልሆነ ብዙ ማስረጃወች ያሉ ከመሆኑም በላይ ትክክልኛ የህዝብ ቆጠራ ለማካሄድ የማይቻልበት ሁኔታ ተፈጥሯል። ምክንያቱ ደግሞ እውነተኛው የህዝብ ቁጥር ከታወቀ በህዝብ ቁጥር እበልጣለሁና ይገባኛል ተብሎ የተያዘው ጥያቄ ውስጥ ሊያስገባ ስለሚችል ነው። በዚህ ላይ ሆን ብሎ ህዝቤ ከቁጥር እንዳይካተት ሆኗል ያለው ስሌት ትክክል አይደለም ትክክለኛ የህብ ቆጠራ ይካሄድ እያለ የሚጠይቅ ህዝብ አለ። ይህ የህዝብ ቆጠራ ጥያቄ ትክክለኛ መልስ የሚሻው አገራዊ ጉዳይ ነው። ፍትሀዊ የፓለቲካ ውክልና ፍትሀዊ የበጀት ቀመርና የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት በሌለበት አገር ሰላምንም ሆነ እድገትን ማረጋገጥ አይቻልም።

በአማራ ክልል የኦሮሞ ብሄር የከሚሴ ልዩ ዞን የአጣየና አካባባቢው ተደጋጋሚ ውድመቶች በዚህ አራት አመት ተኩል ጊዜ ዉስጥ በኦነግ የተደራጀው ሰራዊት ከኦሮሚያ ክልል መንግሥት ድጋፍ በተደጋጋሚ ባልሳሳት ለስድስት ጊዜ ያህል አጣየንና አካባቢውን አውድሟል። ሸዋሮቢትንም እንዲሁ እያወደመ ይገኛል። ይህ የኦነግ ወራሪ ሰራዊት ወረራውን የሚፈፅመው ስልጠናና የሎጅስቲክ ድጋፍ የሚያገኘዉ በአማራ ክልል የኦሮሞ ልዩ ዞን ተብሎ ከተሰየመው ከከሚሴ እየተነሳ መሆኑ በግልፅ ይታወቃል።ለምንድነው አጣየ ሸዋሮቢት ማጀቴ ሰንበቴ የወረራ ማዕከል የሆኑት? መቸም መልሱ የኢትዮጵያን አንድነት ለማስጠበቅ የሚል እንደማይሆን እሙን ነው። ከክልሉ ውጭ የሚኖርው አማራ ላይ በወለጋና በመተከል እየደረሰበት ያለው የዘር ማጥፋት ጭፍጭፋ ሰቆቃ መፍትሄ ሳያገኝ በራሱ ክልል ውስጥ ሀያ በመቶ ለሚሆን ነዋሪ የልዩ አስተዳደር ዞን ፈቅዶ የአማራ ክልልንን ብሎም ኢትዮጵያን የማፍረስ ሂደት እንዴት ዝም ብሎ ይመለከታል? ቢያንስ ለተወሰነ ጊዜ ይህን ልዩ ዞን በክልሉ ስር በቀጥታ እንዲተዳደር ማድረግ መሻሻል ካላሳየ ይህ የኬሚሴ ልዩ ዞን የአማራ ክልል ህዝብ የህልዉና ስጋት ስለሆነ እስከ ማፍረስ የሚደርስ አስተማማኝ እርምጃ መዉሰድ ያስፈልጋል።

የኦሮሚያ ክልል የመስፋፋት ፓሊሲና የወረራ እርምጃወች-የኢትዮጵያ አገራዊ አንድነት ትልቁ ፈተና

በአሁኑ ሰዓት የኢትዮጵያ ትልቁ ፈተና የአገሪቱ ቁልፍ ስልጣን በኦሮሚያ ብልፅግና የተያዘ ሲሆን እነዚህ አመራሮች ደግሞ ኢትዮጵያን ፍትኃዊነት መሰረት በማድረግ ማስተዳደር ሲገባቸው በአፋቸው ኢትዮጵያ አትፈርስም ትበልፃገለች እያሉ በተግባር ግን በግዛት ማስፋት ወረራ ላይ መጠመዳቸው ነው። የወለጋውና የመተከሉ ዘርማጥፋት ጭፍጨፋዎች የአጣየ ደራ ተደጋጋሚ ወረራወች አዲስ አበባና በአዲስ አበባ ዙሪያ የሚደረገው የጥቅለላ እርብርብ ሰፋፊ ቤት ማፍረስና ማፈናቀል ዘመቻዎች በድሬዳዋ ሀረር የሚደረጉ ጥቅለላወች ይህን የመስፋፋት ወረራዎች ፍንትው አድርገው ያሳያሉ። ዋናው ጥያቄ የኢትዮጵያ ህዝብ ይህን ሁሉ እየተመለተ ተገቢውን መልስ በተናጠል ሳይሆን በህብረት ለመስጠት በፍጥነት መዘጋጀት ይኖርበታል። ያቀዱት ከተጠናቀቀ በሁዋላ መጮሁ ምንም አይፈይድም።

ከኦሮሞ ህዝብ የሚጠበቅ ታሪካዊ ኃላፊነት

አብዛኛው የኦሮሞ ህዝብ በግልፅ እንደሚታወቀው ከሌሎች ወንድም ኢትዮጵያውያን ጋር በመልካም ግንኙነት፣ ሃይማኖታዊና ባህላዊ ትስስር ፈጥሮ በሰላም መኖርን የሚመርጥ ህዝብ ነው። በጋብቻ ተሳስሮ ተዋልዶ በስራ ሆነ በመልካም ጉርብትና ተባብሮ እየኖረ ዘመናትን አሳልፏል። እስከሚገባኝ ድረስ የኦሮሞ ህዝብ ግዛት አስፋፉልኝ በግዛት ማስፋፋት ሰበብ የሚፈጠር ግጭት ውስጥ አስገቡኝ ብሎ የጠየቀ አይመስለኝም። መሬት ላይ ያለው በገሃድ እንድሚያሳየው በስሙ ስልጣን ላይ የተሰየሙ ቡድኖችና ተባባሪ የፓለቲካ ኃይሎች የኦሮሞን ህዝብ በሁሉም አቅጣጫ ከሚገኘው የኢትዮጵያ ክልሎች ወይም ህዝብ ጋር ደም እያቃቡት ይገኛሉ። ይህ ለማንም አይጠቅምም። ይህንን የእብደት አካሄድ የኦሮሞ ህዝብ ማስቆም ታሪካዊ ግዴታ አለበት፤ ማስቆም ካልቻለም ከሌላው ኢትዮጵያውያን ጋር በመሆን ሳይዘገይ አሁኑኑ መቃወም አለበት። የለየለት የእርስ በእርስ ጦርነት ከተገባ በሁዋላ ይህን ለማድረግ ቢያስብ ዳፋው ለራሱም ነው የሚተርፈው። አገር ከተበጠበጠ ሰላም ከደፈረሰ ማንም አትራፊ አይሆንም። የትግራይ ህዝብ ህወሓትን ገና በጠዋቱ መግታት ቢችል ወይም ግልፅ ተቃውሞ ቢያሳይ ወይም ድጋፍ ቢነሳቸው ኖሮ ኢትዮጵያ አሁን ካለችበት ቅርቃር ውስጥ አትገባም ነበር። ይህን አሁን ያለውን አገር የማፍረስ ሂደት ለመግታት ብሎም ለማስቆም የኦሮሞ ህዝብ ታሪክ የጣለበትን አደራ ሊወጣ ይገባል።

ሌሎች ባለሃብቶችን በማዳከም የኦሮሞ ባለሃብቶችን ለመፍጠር እየተደረገ ያለው ሰፊ ዘመቻ ያለው መዘዝ መቸም ህወሓት በአገዛዝ ዘመኑ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ በመጠቅለል ኤፍርት በሚባል የንግድ ኩባንያ በመፍጠር ለዚህ ኩባንያ ተቋራጭ እንዲሆኑ ብዙ የትግሬ ባለሀብቶችን ክህግ አሰራር ውጭ በመፍጠር የተለየ መንግስታዊ እገዛ በመስጠት እነርሱ ሌላውን ኢትዮጵያዊ ባለሀብት ከጨዋታ ውጭ በማድረግ በፍጠነት ከበርቴወች መሆን እንደቻሉ ሁሉም የሚያስታውሰው ጉዳይ ነው። ኦህዲዶችም ምንም ሳያስቀሩ የህወሓትን የተንኮል ስራወች በመቅዳት እየስሩ ስለሆነ ባንኩንም አስመጪና ላኪ የንግድ ስራወችን በጠቅላላው ቢዝነሱንና ኢኮኖሚዉን በአብዛኛዉ በኦሮሞ እያስያዙት መሆኑ አሁን የሚታይ መሬት ላይ ያለ ሃቅ ነው። በዚህም ብዙ ኦሮሞወች በፍጥነት ላልተገባ የሀብት ክምችት ባለቤት ለመሆን በቅተዋል። ይህ እየተደረገ ያለው ሌላውን ባለሀብት በማዳከም መሆኑ ግልፅ ነው። ይህ ታንኩንም ባንኩንም ልቆጣጠረው ማለት ለአገር ልማትና እድገት ፀር ከመሆኑም አልፎ ለአገር ሰላምና ደህንነት እጅግ አደገኛ አካሄድ ነው። ህወሓትን ባልጠበቀችው ፍጥነት ከተደላደለችበት የስልጣን መንበር አሺቀንጥሮ ከጣላት ዋነኛ ምክንያቶች ውስጥ አንዱ ይህ የኢኮኖሚ ጥቅለላና አለግባብ የራሴ የምትላቸውን ባለሀብቶች የፈጠረችበት ጉዳይ ነበር። አሁንስ አገር ይዞ እንዳይወድቅ የዘገየ ቢሆንም በአስቸኳይ ማጋለጥና ስማቆም ይገባል።

የከተሞችን ዲሞግራፊ ለመቀየር የተሰራው ስራና አሁንም የቀጠለው ሁኔታ

ኢትዮጵያ ከተሞች ውስጥ የሚኖረው ማህበረሰብ ሆን ተብሎ በእቅድ የአንደኛው ማህበረሰብ በዛ ብሎ እንዲኖር የሌላኛው ማህበረሰብ ቁጥር አነስተኛ እንዲሆን እንዳልተሰራበት የሚታወቅ ነገር ነው። ነገር ግን ኦሮሞው በከተሞች ሆን ትብሎ በስፋት እንዳይኖር እንደተደረገ በመስበክ መፍትሄው ደግሞ በድብቅ የዲሞግራፊ ለውጥ በሁሉም ከተሞች ማድረግ ያስፈልጋል የሚል ውሳኔ ላይ በመድረስ እየተገበሩት ይገኛሉ። በዚህም መሰረት በአዲስ አበባ ብቻ በአንድ ጊዜ ከሶማሌ ክልል የተፈናቀሉ 500 ሺህ ኦሮሞወችን በድብቅ አስፍረዋል። ከዚያም በሁዋላ ከመላው ኦሮሚያ እያመጡ አስፍረዋል: ወይም የአዲስ አበባ የነዋሪነት መታወቂያ እንዲይዙ አድርገዋል። በአንፃሩ ደግሞ ኦሮሞ ያልሆነው በተለይም አማራው ጉራጌው ጋሞው ቤቱን እያፈረሱ በገፍ እያፈናቀሉት ይገኛል። ይህ ስልጣን መከታ አድርጎ የሚደረግ የዲሞግራፊ ቅየራ ዘመቻ ለጊዜው ስኬት መስሎ ቢታያቸዉም እየቆየ ግን ህዝብን ከህዝብ የሚያጋጭ መሆኑ ጥርጥር የለውም።

ህዝብ በረሃብ እየሞተ እንስሳት በሚሊዮኖች እየረገፉ አዲስ ቤተመንግሥት ግንባታና አሳዛኝ የስንዴ ኤክስፓርት ቲያትር ኢትዮጵያ ውስጥ ከወለጋና መተከል ጭፍጨፋ ተርፎ በተሰደደው እንዲሁም የሰሜኑን ጦርነት በመሸሺ የተፈናቀሉ ሚሊዮኖች በተለይም በአማራና አፋር ክልል እርዳታ ሳያገኙ በርሃብ እየሞቱ ያሉ ወገኖች ብዙ ናቸው። የተፈናቃዩ ቁጥር ከአዲስ አበባና አካባቢው በባለጊዜወች መረን የለቀቀ ጥጋብ ቤታቸው በላየቸው ላይ እየፈረሰባቸው በአንዴ ወደ ለማኝነት እንዲወርዱ ተደርገዋል። ይህ ሳያንስ አሁን ደግሞ በቦረና የገባው ርሀብ እንስሳትን ፈጅቶ ለሰው ህይወት መጥፋት መንስኤ እየሆነ ነዉ። ይህ ሁሉ ሲሆን መንግሥት የሚጨነቀው ስለ አዲስ ቤተመንግሥት ግንባታውና ስንዴ ኤክስፓርት ስለማድረጉ ነው። ይህ የለየለት እብደት ስለሆነ ህዝብ ሊያስቆመው ይገባል። ለተራበውና ለተራቆተው ህዝብ እንዲደርስለት ጠንክሮ በመንግሥት ላይ ግፊት ማድረግ ይጠበቅበታል። ይህ መንግሥትን ከስልጣን ማውረድ የሚያስችል ቁጣ የሚፈጥር ጉድይ ካልሆነ ምን ሲፈጠር ነው ቁጣ የሚፈጠረው?

የህወሓትና የኦሮሚያ ብልፅግና አዲስ ወዳጅነትና መዘዙ

ህወሓት ለሀያ ሰባት አመታት በሁሉም የኢትዮጵያ ሕዝብ በተለይም በአማራና ኦሮሞወች ላይ ያደረሰዉ ኅልቆ መሳፍርት የሌለዉ ግፍ ተዘንግቶ በመከላከያ ሰራዊት ያደረሰዉ ዘግናኝ ጥቃት በአማራና አፋር ክልሎች የፈፀመዉ ተደጋጋሚ ወረራና በንፁሀን ላይ ያደረሰዉ መጠነ ሰፊ ጭፍጨፉ ተረስቶ የኦሮሚያ ብልፅግና የፖለቲካ አሰላለፉን ፖርላማዉ ሺብርተኛ ብሎ ከፈረጀዉ ህወሓት ጋር አድርጏል።ሁለቱ በጋራ በመሆን አማራዉ የማንነቴ መገለጫ ናቸዉ ያላቸዉን ወልቃይትና ራያን በጦርነት ወደ ትግራይ ዳግም ለመዉሰድ እየሰሩ መሆናቸዉ ተደርሶበታል። ህወሓትም በበኩሉ የኦሮሚያ ክልልን የግዛት ማስፉት ዘመቻዉን ያግዛል። ወደ አንድ ሚሊየን ህዝብ የቀጠፈዉ የሰሜኑ ጦርነት በአግባቡ ባለመቋጨቱ እዚህ ላይ ተደርሷል።

ይህ አደገኛ የፖለቲካ ጥምረት በህዝብ የተባበረ ትግል መምከን አለበት ህወሓትንና ከሞት አፉፍ ያዳናትን የኦሮሚያ ብልፅግና አብሮ ማሰናበት የግድ ይላል። ህዝብ ተባብሮ በአስቸኳይ ይህን ካላደረገ ግን በኢትዮጵያ ፍርስራሺ ላይ ሁለት አዲስ አገሮች ሲፈጠሩ ለማየት በግዴለሺነት እየጠበቀ መሆኑን ያሳያል ማለት ነዉ። ኢትዮጵያ ህዝብ ይህን አገር የማፍረስ ግስጋሴ ዝም ብሎ ያያል ብየ አላምንም። ነገር ግን በተግባር በፍጥነት ዉድ እናት አገሩን ከመፍረስ ለመታደግ መንቀሳቀስ ይኖርበታል።

ማጠቃለያ

ኢትዮጵያ አትፈርስም እያሉ በየመድረኩ የሚለፍፉት ፈፅሞ ሀሰትና ማዳናገሪያ ስልት ነው። በተጨባጭ ግን በተጠናና ግብ በተቀመጠለት አካሄድ ኢትዮጵያን እያፈረሷት ነው። የምናወራዉ ስለ መልክዓ ምድሩ አይደለም። በውስጧ ስላለው ህዝብ ቋንቋዉ ሃይማኖቱ ታሪኩ ወዘተ ነው። ኢትዮጵያን በመመስረትና ከጠላት በመጠበቅ ቀዳሚ ቦታ ያለውን የአማራ ነገድ መጤ ሰፋሪ እያሉ መጨፍጨፍ፣ የአገሪቱ ዋነኛ መግባቢያ የሆነውን አማርኛ ቋንቋን ለማጥፋት በግልፅ እየተሰራ፣ ኢትዮጵያውያንን ለትምህርት ያበቃች ፊደልና ቁጥር ሰርታ ያበረከተች የአገሪቱን ህዝብ ግማሽ ቁጥር ያለዉን ምዕመን አንድ አድርጋ መንፈሳዊ አገልግሎት እየሰጠች ያለች፣ አገር ሲወረር ታቦታትን ይዛ አብራ በመዝመት ለድል የምታበቃን አገራዊ ተቋም (የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያንን) እያሳደድህ፣ የኢትዮጵያ ታሪክ ታሪኬ አይደለም፣ አገሪቱ እንደገና ለእኛ እንድትመች ሆና መሰራት አለባት እያልህ ያደጉ ከተሞችንና ስትራቴጂ ቦታዎችን ወደ ራስ ለመጠቅለል እየተሯሯጥህ ኢትዮጵያ አትፈርስም ለማለት እንዴት ይቻላል? መልሱ አይቻልም ነው። የኢትዮጵያን አንድ አገርነት ከተቀበልህ ይህ ሁሉ የእኔ ይሁን የሚለው ሩጫ ለምን አስፈለገ?

ህዝቡ በግልፅ መገንዘብ ያለበት ነገር ኢትዮጵያን ቀስ በቀስ በስልት እያፈረሷት መሆኑን ተረድቶ ለማስቆም ጠንክሮ መታገል አለበት። ለመብቱ ለአገር እንድነት ለታሪኩ መከበር መቆም ያለበት ሁሉም ኢትዮጵያዊ ነው። መፍትሄው መለስ ዜናዊ ኢትዮጵያን አፍርሶ ታላቋን ትግራይን ለመመስረት እንዲያስችለው የቀረፀውን ህገ መንግሥት ማሻሻል ሳይሆን ህዝብ የመከረበትና የተሳተፈበት በአዲስ ህገ መንግሥት በመለወጥና የአፓርታይድ ክልል አወቃቀርን አስወግዶ በትክክለኛ የአስተዳደር አወቃቀር መተካት ነው። ይህ አዲስ ህገ መንግሥት የሚዘጋጀው የስርዓት ለውጥ ከመጣ በኋላ መሆን ይኖርበታል። አሁን ያለው ተረኛው ኃይል ውስን የሆኑ ማሻሻወች ሊያደርግ ደፋ ቀና እያለ መሆኑ ይስተዋላል። ይህ ግን ከመሰረቱ ችግሩን ስለማይፈታ በዚህ ማደናገሪያ መዘናጋት አይገባም። ህዝቡ ለእውነተኛ የስርዓት ለውጥ አጥብቆ መታገል ይኖርበታል። አለበለዚያ አይኑ ስር ህወሓትና ኦነግ ኢትዮጵያን አፍርሰው ሁለት አዲስ አገራት ማለትም ታላቂቷን ትግራይና ታላቂቷን ኦሮሚያ ሲፈጥሩ በቁጭትና በሀዘን መመልከት ብቻ ይሆናል። በብዙ ትውልድ መስዋእትነት በአስተዋይ መሪወችና የሃይማኖት አባቶች አርበኞች መስዋእትነት የተገነባች ጥንታዊት ሀገር በጥቂት አገር አፍራሽ ባንዳወች ስትፈርስ ዝም ብሎ ማየት ትውልድን ወደማያበራ ጦርነት መክተት መሆኑን በመረዳት ሁሉም ኢትዮጵያዊ የሚጠበቅበትን ሁሉ ለማድረግ መዘጋጀት አለበት።

በተለይም ከህወሓትና ኦነግ ቀጥተኛ የሆነ የህልውና ፈተና ተደቅኖበት የሚገኘው ከህዝብ አማራው ከሃይማኖት ኦርቶዶክሱ እንዲሁም የሙስሊሙ ማህበረሰብ ህልውናውን ለማስከበር የሚችልና የጠላቶቹን እቅድ ሊያመክን የሚችል ቁርጠኛ ትግል ማድረግ ይጠበቅበታል። የዚህ ኢትዮጵያን የማፍረስ ሴራ ዋነኛ አስፈፃሚ ሆኖ እየሰራ ያለውን የኦሮሞ ብልፅግናን እና መሪውን ጠቅላይ ሚኒስቴር በአስቸኳይ ከስልጣን በማውረድ ለእውነተኛ የስርዓት ለውጥ የሽግግር ጉዞ ሊያበቁ በሚችሉ ሰዎች መተካት ለነገ ሊባል የማይገባ በጣም አንገብጋቢ ጉዳይ ነው። ሁሉም ሰው ከዚህ ፅሁፍም ሆነ ከነባራዊ ሁኔታው ሊረዳው እንደሚችለው ኢትዮጵያ ትልቅ አደጋ ላይ ትገኛለች። የኢትዮጵያ ነገር በጣም ያሳስበኛል። በዘመኔ ሶቭየት ህብረትን የመሰለ ልዕለ ኃያል አገር ፈርሶ ወደ 15 አገርነት ሲበተን እዚያው ኖሬ አይቸዋለሁ። አሁን ኢትዮጵያ ያለችበት ሁኔታ ሶቭየት ህብረት ከመፍረሱ በፊት ከነበሩትሁለት ሶስት አመታት ጋር ይመሳሰላል። ዩጎዝላቪያም የፈረሰውና ወደ 6 አገሮች የተበተነው በተመሳሳይ ሁኔታ ነው። ልዩነቱ ዩጎዝላቪያ በጦርነት ጭምር የተካሄደ መለያየት መሆኑ ነው። ለሁለቱም አገሮች መፍረስ የምዕራባዊያን እጅ አለበት። ኢትዮጵያን አንድ እና ነፃ አገር ሆና በራሱዋ መንገድ እንዳትሰለጥን የሚሰሩ ብዙ ስውር እጆች አሉ። ስለዚህ ኢትዮጵያውያን እገራቸውን ለመታደግ ቆርጠው መስራት ይጠበቅባቸዋል።

Publisher’s note: views in the article reflect the views of the writer, not the views of tbf.2tbf.org 



Comments

Popular posts from this blog

"ከአሁን በሆላ ፋኖ ወደ አንድነት መምጣት አለባቸው የሚባለው አካሄድ አይሰራም" :: በወዳጄ/ቤተ አማራ ወሎ

ከአሁን  በሆላ  ፋኖ  ወደ  አንድነት    መምጣት  አለባቸው  የሚባለው  አካሄድ  አይሰራም::  ክህደት   ከተፈፀመ  በሆላ  አንዱ  ቡድን  ከሌላው  ስር  ሆኖ  ይቀጥላል  ማለት  የማይቻል   ነው::  ምክኒያቱም 1ኛ:- 27  ቀን  ቁጪ  ብለው   መክረዋል :: እያንዳንዱ  አደረጃጄት  ሰነድ  ፅፈው  አቅርበዋል::  በቀረበው  ሰነድ  ላይ  ከፍተኛ  ውይይት  ተደርጎበት  የሚወድቀው  ወድቆ  የሚፈለገው  ፀድቋል::ቃለ  መሀላ  ፈፅመው   ወደ  ምርጫ   ለመግባት  ተስማምተዋል:: እጃቸውን  አውጥተው   ከመረጡ  በሆላ    ግን    "ጨዋታ  ፈረሰ  ዳቦ  ተቆረሰ"   የሚል  የህፃን  ልጂ  ጨዋታ  ውስጥ  መግባት   የአማራን  ህዝብም  ሆነ  የፋኖን  ትግል  መናቅ  ነው:: ይህ  አልበቃ  ብሎ   "ምርጫው  ከኛ  እውቅና  ውጪ  ነው  እኛ  አናውቀውም"  የሚል   የውሸት    የህፃን  ልጂ  ፕሮፓጋንዳ...

ስርነቀል ለውጥ ማምጣት የአማራ ብሄርተኝነት የህልውና ትግል ብቸኛ ግብ ነው። በ Alen Kassahun

ምስሉ ጸሃፊውን አይወክልም፡፤ ከ50 አመታት በላይ የተተከለውንና በተግባር እየተፈፀመ ያለውን አማራን ማጥፋትና ኢትዮጵያን ማፍረስ ከስሩ በመንቀል #4ኪሎን ተቆጣጥሮ ስርነቀል ለውጥ ማምጣት የአማራ ብሄርተኝነት የህልውና ትግል ብቸኛ ግብ ነው። ፋኖ በሚያደርገው የህልውና ትግል አማራ ጠልነት የወለደውን የአማራን ዘር ማጥፋት፤ ማፅዳት፤ የሰባዊ መብት ጥሰትና አገር ማፍረስ አለምአቀፍ ወንጀል ከስሩ ነቅሎ ሊቀብረው #በዋዜማው ላይ እንገኛለን። ስለሆነም ፋኖ እያደረገ ያለውን የህልውና ትግል #በድል እንዳይቋጭ  በድርድር፣ በእርቅና በምክክር ሰበብ የፋኖን ድል ለመቀልበስና ለመንጠቅ ከአሜሪካ እስከ አዲስ አበባና መቀሌ ድረስ በሚሸረብ ሴራ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ፤ በስልታዊ አማራነትም ሆነ በአማራ ጠልነት የተሰለፉ ቅጥረኞች ደፋ ቀና እያሉ እንደሚገኙ ግልፅ ነው። ፋኖ #አራት ኪሎን በመቆጣጠር ስርነቀል ለውጥ ለማወጅ በድል ዋዜማ ላይ ሆኖ እያደረገ ያለውን የመጨረሻውን ትንቅንቅ ለማሰናከልና ድሉን ለመሸጥ ተቀጥራችሁ ስለ ድርድር፣ ሽግግር፣ እርቅ፣ ውይይትና በመሳሰሉ አጀንዳዎች በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ እየሰሩ የሚገኙ ቅጥረኞችን ከቀጣሪዎች እኩል ማሸነፍና ማስወገድ የህልውና ትግላችን ብቻኛ አማራጭ መሆኑ ለማንም ግልፅ ሊሆን ይገባል። ስለሆነም የዜግነት ፓለቲካ አቀንቃኝ የ3ኛ ወገን ቅጥረኞችን ከጀርባው አሰልፎ የአማራን ብሄርተኝነት የማድፈቅ አጀንዳቸውን አዝሎ ከአማራ ህልውና ትግል መሀል የተገኘው #እስክንድር ነጋ ከአማራ ህልውና ትግል ጓዙን ጠቅልሎ እንዲወጣ ማድረግ ለነገ የሚባል አይደለም። የእስክንድር ነጋ #የእየሱስ ክርስቶስነት ገፀ ባህሪ በሂደት እየተገፈፈ መምጣት አማራ ጠል ሀይሎችን ወደ እቅድ ሁለት ሴራ እንዲገቡ እያስገደደ በመሆኑ የአማራ ብሄርተኛ #እስክንድ...

አለም አቀፍ የፋኖ ድጋፍ አስተባባሪ ኮሚቴ ነኝ የሚለው ቡድን ዓላማ ምንድነው ? በወንድወሰን ተክሉ

ይህ ምስል ጸሃፊውን አይወክልም! «...አማራ ለ450 ዓመታ መንፈሱ የተሰበረ ገበሮ ሕዝብ ነው..» ሀብታሙ ተገኝ (ፕ/ር) « እኔ እስክንድር  የአማራ ሕዝብ ከደረሰበት የህልውና አደጋ እኩል የሚሆን ዓላማ አለው ብዬ አላምንም» አቻምየለህ ታምሩ፤ አለም አቀፍ የፋኖ ድጋፍ አስተባባሪ ኮሚቴ ነኝ የሚለው ቡድን ዓላማ ምንድነው ? በወንድወሰን ተክሉ እራሱን አለም አቀፍ የፋኖ ድጋፍ አስተባባሪ ኮሚቴ ነኝ የሚለው ቡድን የዙም ውይይት ፕሮግራም ክፍል ሁለትን የተመለከተ ምልክታ:- ባለፈው  ወር ብቻ ሳይሆን ባለፈው ዓመት ዴሴምበር 2023 ( ዛሬ ጃንዋሪ 1 ቀን 2024 ነን)  እራሱን አለም አቀፍ የፋኖ ድጋፍ አሰባሳቢ ኮሚቴ ብሎ የሚጠራው ቡድን «ጸረ አማራ ኢትዮጲያዊነት» በሚል አርእስት ስር ሀብታሙ ተገኝ (ፕ/ር) ዋና ተናጋሪ ተጋባዥ የሆነበትን  የዙም ውይይት አካሂዶ የነበረ ሲሆን የዚህ ውይይት ክፍል ሁለት  ባሳለፍነው ወር ዴሴምበር 23ቀን በማዘጋጀት አቻምየለህ ታምሩና ሀብታሙ ተገኝ (ፕ/ር) ተናጋሪ እንግዳ በማድረግ አካሂዷል። በእርግጥ  ከዚህ ከሁለተኛው የውይይት ፕሮግራም በፊት በተክሌ ይሻው በኩል የዙም ሊንክ ተልክሎኝ በሰዓት ጥበት ምክንያት መገኘት ባልችልም ዛሬ ግን በቻናላቸው ላይ የጫኑትን ይህን ክፍል ሁለት ውይይት ከተመለከትኩ በኋላ ይህን ምልክታዬን  አንባቢው ሊረዳ በሚያስችል መልኩ አንድ ሰዓት ከሰላሳ ደቂቃ የፈጀን ውይይት ይዘት በመጭመቅ እንደሚከተለው አቅርቤያለሁ። ይህ ምስል ጸሃፊውን አይወክልም! 1ኛ - ውይይቱን አዘጋጅን ማንነት በተመለከተ፦  አለም አቀፍ የፋኖ ድጋፍ አስተባባሪ ኮሚቴ ባለፈው መስከረም ወር ላይ  በጌታቸው በየነ ሰብሳቢነት ተመሰረትኩ ብሎ እራሱን ያስተዋወቀ ሲ...